"የስፖርት ህይወቴን የጀመርኩት በእግር ኳስ ጫወታ ነው" አትሌት ገለቴ

96
አዲስ አበባ ግንቦት 17/2010 ""የስፖርት ህይወቴን የጀመርኩት በእግር ኳስ ጫወታ ነው"  ስትል ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ገለቴ ቡርቃ ገለጸች። በመካከለኛና በረጅም ርቀት ውድድር የምትታወቀውና የትኩረት አቅጣጫዋን ወደ ማራቶን ያዞረችው የ32 ዓመቷ አትሌት ገለቴ ቡርቃ ስለ አትሌቲክስ ህይወቷ ከዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ጋር ቆይታ አድርጋለች። 'የስፖርት ህይወቴን የጀመርኩት እግር ኳስ በመጫወት ነው። ጥሩ ተጫዋች ነበርኩ ከኳስ ጋር ያለኝ እንቅስቃሴ ፈጣንና ብዙ ጎሎችንም አስቆጥር ነበር' ስትል የገለጸችው አትሌት ገለቴ የአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ መሳተፍ በመጀመሯ የተነሳ ምርጫዋ ወደ አትሌቲክስ መሳቡን ተናግራለች። "እኔ እስከማስታውሰው ሩጫ የህይወቴ አንድ አካል ነው በምኖርበት መንደር ውስጥ ከቤት ወደ ትምህርት ቤት ከትምህርት ቤት ወደ ቤት እየሮጥኩ እሄድ ነበር" ስትል አትሌት ገለቴ ታስታውሳለች። ታዳጊ እያለች ተምሳሌት አድርጋ የምትከተላት አትሌት ደራርቴ ቱሉ እንደነበረች የምትናገረው ገለቴ 'ደራርቱ ትልቅ ተነሳሽነት ትፈጥርልኝ ነበር። ሁልጊዜ እሷን መሆን እፈልግ ነበር' ስትለ አስታውሳለች። የመሮጥና የመወዳደር አቅሟ እየተሻሻለ ሲመጣ እንደ አትሌት ደራርቱ ፕሮፌሽናል ሯጭ መሆን እንደምትችል በመረዳቷ  አትሌቲክስ ጥሩ ምርጫዋ መሆኑን ተናግራለች። ሩጫ ቀላል ስፖርት ሳይሆን ጠንካራ ስራ የሚጠይቅና ድካም ያለው መሆኑን ገልጻ ጠንካራ ልምምድ ለማድረግ መስዋዕትነት የሚያስከፍልና የአሸናፊነት ስነ ልቦና መላበስን የሚፈልግ እንደሆነ ገልጻለች። የአሸናፊነት ስነልቦና ለመላበስ ከራሷ ጋር የምታደርገው ትግል ጠንካራ መሆኑን ጠቁማለች። 'የምሮጠው ለብዙ ምክንያቶች ነው፤ አንደኛው አትሌቲክስ ትልቅ ስፖርትና እጅጉን አዝናኝ መሆኑ፣ ሁሉንም ውድድር ማሸነፍ ባይቻልም ከማሸነፋቸው ውድድሮች የማገኘው ደስታና እርካታ ጥሜን የሚያረካና ሁልጊዜ እንድነሳሳ የሚያደርገኝ ነው' ስትል አትሌት ገለቴ ተናግራለች። ፕሮፌሽናል ሯጭ መሆኗ የፋይናንስ ጥቅሞችን እንድታገኝ ስላስቻላት ቤተሰቦቿን ለመርዳት ያገዛት መሆኑን አመልክታለች። 'ሩጫ በዓለም ላይ በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ ሰዎች ጋር እንድገናኝና በህይወቴ መረጋጋት፣ ጤናና ሰላም እንዳገኝ አድርጎኛል' በማለት አትሌት ገለቴ ታስረዳለች። የሩጫ ስፖርት ጤናማ የሆነ ህይወት ለመምራት ወሳኝ በመሆኑ ሰዎች እንዲሮጡ የምታበረታታው አትሌት ገለቴ በስፖርቱ ያላትን ሰፊ ተሞክሮ አካፍላለች። 'የሩጫ ህይወትን መከተሌ በጣም ጥሩ ምርጫ ነው' በሚል መልዕክት አትሌት ገለቴ ቡርቃ ከዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ጋር የነበራተን ቆይታ አጠናቃለች።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም