ባለቤቱንና ሁለት ልጆቹን የገደለው በእድሜ ልክ እስራት ተቀጣ

86
ጎባ ታህሳስ 16/2011 የባለቤቱንና የሁለት ልጆቹን ህይወት ያጠፋው ግለሰብ በእድሜ ልክ እስራት እንዲቀጣ የተወሰነበት መሆኑን የባሌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት  አስታወቀ፡፡ የፍርድ ውሳኔው አስተማሪ አይደለም ሲሉ አስተያያት ሰጪዎች ተናግረዋል ፡፡ ሁሴን ተማም የተባለው ግለሰብ  ግድያውን ፈጽሟል የተባለው ህዳር 13/2011 ዓ.ም. እኩለ ሌሊት ላይ በባሌ ዞን ጊኒር ወረዳ አቦሰራ ቀበሌ ልዩ ስሙ ኡረኔ ሼካ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መኖሪያ ቤቱ ውስጥ ነው፡፡ ግለሰቡ ድርጊቱን በአሰቃቂ ሁኔታ  እንደፈጸመና ይህም ባለቤቱ  ከሌላ ሰው ጋር የፍቅር ግንኙነት አላት ብሎ በመጠራጠሩና በቅናት መንፈስ ተነሳስቶ እንደሆነ የአቃቤ ሀግ የክስ መዝገብ ያመላክታል ። የዞኑ  ከፍተኛ ፍርድ  ቤት ዳኛ አቶ ተስፋዬ ሄጬ እንዳስረዱት ግለሰቡ በባለቤቱና በልጆቹ ላይ የፈጸመው አሰቃቂ የግድያ ወንጀል በሰውና በህክምና ማስረጃ ተረጋግጦበታል፡፡ ተከሳሹ ክሱን እንዲከላከል እድሉ ቢሰጠውም አልቻለም ። አቃቤ ህግ በተከሳሹ ላይ የቅጣት ማክበጃ ሀሳብ ሲያቀርብ ተከሳሹ ድርጊቱን የፈጸመው በጭካኔ መንፈስ  የገዛ ቤተሰቦቹ በተኙበት ጨለማን ተገን በማድረግ መሆኑንና ከገደላቸው በኋላም በብርድ ልብስ ጠቅልሎ ለመደበቅ ጥረት ማድረጉን አስረድቷል ። እንዲሁም እራሳቸውን መከላከል የማይችሉ የሶስት ዓመትና የስድስት ወር እድሜ ያላቸውን ልጆቹን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደሉ ለውሳኔ ማክበጃ አቃቤ ህግ ካቀረባቸው ሀሳቦች መካከል ተጠቃሾች ናቸው ፡፡ የተከሳሹ ጠበቃ በበኩሉ ተከሳሹ ከዚህ በፊት የወንጀል ሪከርድ የሌለበት መሆኑንና የፈጸመውን ድርጊት በማመኑ ለውሳኔ ማቅለያነት እንዲሆንለት  ሀሳብ አቅርቧል፡፡ ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት  ከግራና ቀኝ የቀረበለትን  ሀሳብ ከመረመረ በኋላ ዛሬ በዋለው ችሎት በእድሜ ልክ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ አስተላልፏል ። በፍርድ ሂደቱ ላይ የተገኙት የተበዳይ ወላጅ እናት  ወይዘሮ ፋጦ መሐመድ እንደተናገሩት ፖሊስ ወንጀለኛውን ይዞ ፍርድ እንዲያገኝ መደረጉን አድንቀው በተሰጠው ውሳኔ ግን አለመርካታቸውን ተናግረዋል፡፡ የፍርድ ውሳኔው ሌሎችንም በሚያስተምር መልኩ የሞት ቅጣት መሆን ነበረበት ብለዋል። ፍርድ ቤቶች በየቦታው አሰቃቂ ወንጀል በሚፈጽሙ ግለሰቦች ላይ የሚሰጡት የፍርድ ውሳኔ ተመጣጣኝ ባለመሆኑ የወንጀል ድርጊቶች እየተበራከቱ በመምጣታቸው ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ያመለከቱት ደግሞ  የፍርድ ውሳኔውን የተከታተሉት የሮቤ ከተማ ነዋሪ አቶ አብዳ ሀሰን ናቸው ፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን ድርጊቱ አሰቃቂ የግድያ ወንጀል ቢሆንም ተከሳሹ ከአሁን በፊት በወንጀል ተከሶ የማያውቅ መሆኑን በማቅለያነት በመውሰድ የእድሜ ልክ እስራት እንደበየነበት አስረድቷል ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም