ሚኒስቴሩ በዩኒቨርሲቲዎች የሚስተዋሉ ችግሮችን የአጭር ጊዜ እቅድ አውጥቶ እንዲፈታ አቅጣጫ ተሰጠው

84
አዲስ አበባ ታህሳስ 16/2011 የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የአጭር ጊዜ እቅድ በማውጣት በዩኒቨርስቲዎች እያጋጠመ ያለውን የመማር ማስተማር መስተጓጎል እንዲፈታ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ። በምክር ቤቱ የሰው ሃብትና ቴክኖሎጂ ቋሚ ኮሚቴ የሚኒስቴሩን የመቶ ቀናት እቅድ አፈጻጸምና የ2011 እቅድ ሪፖርት አዳምጧል። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ወልደ ማሪያም ሚኒስቴሩ በ100 ቀናት እቅዱ ያከናወናቸውን ስራዎች ለምክር ቤቱ አቅርበዋል። በሪፖርታቸውም ተቋሙ እራሱን በማደራጀት፣ ለዩኒቨርስርቲ ተማሪዎች በታዋቂ ግለሰቦችና በምሁራን አነቃቂ ንግግሮችን ማቅረብ፣ እየተፈጠሩ ላሉ ብጥብጦች ውይይቶችን በማድረግ መፍትሄ ለማበጀት የተከናወኑ ተግባራትን አስረድተዋል። ይሁን እንጂ ሪፖርቱ ከወራት በፊት በዩኒቨርስቲዎች ስምሪት ተደርጎ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር በውይይት የተለዩ ችግሮችና የተወሰዱ እርምጃዎችን ሪፖርቱ አላመላከተም በማለት ከቋሚ ኮሚቴ አባላት ጥያቄ ተነስቷል። የእቅዱ አፈጻጸም "በሂደት ላይ ነው" ከማለት ውጪ የተለዩ ችግሮችና የተወሰዱ የመፍትሄ ርምጃዎችን አላመላከተም ሲሉም ጠይቀዋል። በመሆኑም ችግሮች ተለይተው በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ሊፈቱ እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል። የሰው ሃብትና ቴክኖሎጂ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ እምዬ ቢተው ከአገራዊ ለውጡ ጋር አብሮ ለመራመድ የመማር ማስተማሩ ሰላማዊ እንዲሆን መስራት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። በዩኒቨርስቲዎች ለቅሬታ ምንጭ እየሆኑ ካሉ ችግሮች መካከል የምግብ፣የግዥና ሌሎች የግብአት አቅርቦትን መነሻ በማድረግ ልዩ እቅድ በማውጣት መሰራት እንዳለበትም አሳስበዋል። ሚኒስቴሩ በዚሁ ዙሪያ ልዩ እቅድ አውጥቶ በተፋጠነ ሁኔታ እንዲተገብርና እቅዱንም ለቋሚ ኮሚቴው እንዲልክ ትእዛዝ ሰጥተዋል። በሪፖርቱ ከውይይት ግኝት በኋላ የተፈቱ ችግሮችን ያካተተ ሪፖርት ቢጠበቅም የቀረበ ነገር የለም በማለት ሰብሳቢዋ ተችተዋል። በመሆኑም ተቋሙ በልዩ እቅድ ችግሮችን ለመፍታት ካልሰራ ተጨማሪ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ ያሉት ወይዘሮ እምዬ በቀጣይ በልዩ ትኩረት እንዲሰራ አሳስበዋል። ሚኒስትሯም ከቋሚ ኮሚቴ አባላት የተነሱትን ምክረ ሀሳቦችና ማስተካከያዎች ተቀብለው ለማስተካከል ቃል ገብተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም