በደብረታቦር ዩኒቨርስቲ የተከሰተው አለመረጋጋት ወደ ሰላማዊ ሁኔታ ተመለሰ

91
ባህርዳር ታህሳስ16/2011 በደብረታቦር ዩኒቨርስቲ  ተከስቶ የነበረው አለመረጋጋት ወደ ሰላማዊ ሁኔታ መመለሱን የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት አስታወቁ። የዩኒቨርስቲው ፕሬዝደንት  ዶክተር አነጋግረኝ ጋሻው ለኢዜአ በስልክ እንደገለጹት ችግሩ የተከሰተው ታህሳስ 14/2011ዓ.ም. ምሽት ሶስት ሰዓት አካባቢ ለጊዜው ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ የጥበቃ ሰራተኛ በተኮሰው ጥይት የአንድ ተማሪ ህይወት ማለፉን ተከትሎ ነው፡፡ ሌላም አንድ ተማሪ ቆስሎ   ወደ ፈለገ ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል መላኩን አመልክተው በተከሰተው ችግር ምክንያት  ከግቢው ወጥተው የነበሩ ተማሪዎችን እንዲመለሱ በማድረግና በማወያየት አሁን ላይ አንፃራዊ ሰላም መስፈኑን አስታውቀዋል፡፡ ከተማሪዎች ጋር የተጀመረው ውይይት ከአካባቢው የኃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎችን በማሳተፍ እንደሚቀጠል የዩኒቨርስቲው ፕሬዝደንት  አመልክተዋል፡፡ " የተቋረጠው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራም ፈጥኖ እንዲጀምር ተማሪዎችን የማግባባትና የማሳመን ስራ ይከናወናል" ብለዋል። በጥበቃ ሰራተኛው ህይወቱ ያለፈው በደቡብ ጎንደር ዞን የደራ ሃሙሲት ተወላጅ የሆነው ተማሪ አስከሬንም ወደ ትውልድ አካባቢው መላኩን ጠቅሰዋል። ጉዳት ያደረሰው የጥበቃ ሰራተኛም ለጊዜው ከአካባቢው ቢሰወርም የፀጥታ አካላት በቁጥጥር ስር ለማዋል እየሰሩ መሆናቸውንም የዩኒቨርስቲው ፕሬዝደንት ጨምረው ገልጸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም