በቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ መከላከያና ሙገር ሲሚንቶ ድል ቀንቷቸዋል

57
አዲስ ታህሳስ 15/2011 መከላከያና ሙገር ሲሚንቶ በ2011 ዓ.ም ሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ አሸነፉ። የፕሪሚየር ሊጉ ሦስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ተካሂደዋል። ቅዳሜ በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲዮም በተደረገ ጨዋታ መከላከያ በሦስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጣና ባህርዳርን 3 ለባዶ በሆነ ውጤት በማሸነፍ በሊጉ ሦስተኛ ድሉን አስመዝግቧል። መከላከያ ከዚህ በፊት ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ፌደራል ማረሚያ ቤቶችንና አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽን ማሸነፉ ይታወሳል። ትናንት በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲዮም በተደረገ ጨዋታ ሙገር ሲሚንቶ በአምስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አዲስ አበባ ፖሊስን 3 ለ 2 በማሸነፍ ሦስተኛ ድሉን ማስመዝገብ ችሏል። ሙገር ሲሚንቶ ከዚህ በፊት ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ፌደራል ማረሚያ ቤቶችንና መዳወላቡ ዩኒቨርስቲን ማሸነፉ ይታወሳል። እንዲሁም ፌደራል ማረሚያ ቤቶች በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽን 3 ለ 1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ከሁለት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ የመጀመሪያ ድሉን አግኝቷል። በአንጻሩ በፕሪሚየር ሊጉ አዲስ ተሳታፊ የሆነው አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም። ክልል በተደረገ አንድ ጨዋታ ሶዶ የአምናው የሊጉ አሸናፊ ወላይታ ድቻ በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መዳወላቡ ዩኒቨርስቲን 3ለ 1 በማሸነፍ በሊጉ ሁለተኛ ድሉን አስመዝግቧል። ስምንት ክለቦች እየተሳተፉበት በሚገኘው የሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ አራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች እስከ ታህሳስ 21 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ የሚካሄዱ ሲሆን በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲዮም ሙገር ሲሚንቶና ወላይታ ዲቻ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም