ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ወደ ሱዳን አመሩ

163
አዲስ አበባ ሚያዚያ 24/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለሁለት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ሱዳን አቀኑ። ዶክተር አብይ አህመድ ከሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር ጋር በሁለትዮሽና በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ቀጥሎም ከኢትዮ-ሱዳን የንግድ ማኅበረሰብ ጋር ወይይት ያደርጋሉ፤ የመስክ ጉብኝትም ይኖራቸዋል ተብሏል። የኢትዮጵያና ጎረቤት አገር ሱዳን ግንኙነት የተጀመረው በአራተኛው ክፍለ ዘመን በአክሱምና በሱዳኑ የሜሮይ ሥልጣኔ በነበረበት ወቅት ነበር። ከዛም ጊዜ አንስቶ የሁለቱ አገራት ግንኙነት በተለይም በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ ጠንካራና ለአሁኑ አጋርነት መሰረት መጣሉን መረጃዎች ያሳያሉ። አገራቱ ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትም ከጀመሩ በኋላም ያሏቸውን ማኅበራዊ ግንኙነቶች በኢኮኖሚና በፖለቲካ መስክ አጠናክረውታል። በተለይም በአገራት መሪዎችና በከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ደረጃ የተደረጉት ይፋዊ የሥራ ጉብኝቶችም ለዚሁ ግንኙነት መዳበር አበርክቷቸው የላቀ ነበር። በምጣኔ ኃብት መስኮች ላይ ያሏቸውን የትብብር አድማሶች ለማስፋት የጋራ የኢኮኖሚ ኮሚሽንም በማቋቋም እየሰሩ ይገኛሉ። ይህንም ስትራቴጂካዊ አጋርነትም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2013 ጀምሮ የተለያዩ የስምምነት ማዕቀፎችን በማጽደቅም ጭምር  አጽንተውታል። የንግዱ ዘርፍ ግንኙነትም፤ ኢትዮጵያ የግብርና ምርቶችን ወደ ሱዳን በመላክ በአንጻሩ ሱዳን የነዳጅ ጋዝን  ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ላይ ያመዘነ ነው። ለአብነትም ባለፈው ዓመት የሁለቱ አገራት የንግድ ልውውጥ 300 ሚሊዮን ዶላር መድረሱን ነው መረጃዎች የሚያሳዩት። ይሁንና ኢትዮጵያ በየዓመቱ 100 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለሱዳን በመሸጥ በየዓመቱ 80 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢም ታስገባለች። በተጓዳኝ ከ800 በላይ የሱዳን ባለኃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ ተሰማርተዋል። በዚህም በኢትዮጵያ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ ከሚጠሩ አገራት ተርታ ሱዳን አንዷ መሆኗ ታውቋል። ኢትዮጵያና ሱዳን በመንገድ የተገናኙ አገራት ሲሆኑ በቀጣይ ደግሞ ልክ እንደ ጅቡቲ በባቡር መስመር ለመተሳሰር እቅድ መኖሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል። በፖለቲካውም መስክ የጋራ አቋምን በመያዝ በአፍሪካ ቀንድና አከባቢው ላይ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ቀጠናዊ ትብብር አላቸው። ኢትዮጵያና ሱዳን 'የታላቁ ህዳሴ ግድብ ለቀጠናው አገራት ምጣኔ ኃብታዊ ውህደት ያመጣል' በማለትም የጋራ አቋም የሚያንጻባርቁ አገራትም ናቸው። ያም ብቻ ሳይሆን ግድቡ ለቀጠናው አገራትም ጭምር የተናጠል ጥቅም እንደሚሰጥ በጽኑ ያምናሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሥልጣን ላይ ከወጡ በኋላ በውጭ አገር ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ሲያደርጉ ይህ ሁለተኛው ነው። በአፍሪካ በሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ ላይ የምትገኘው ሱዳን፤ በቆዳ ስፋቷ ከአፍሪካ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ከ41 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይዛለች። ጎረቤታሞቹ ኢትዮጵያና ሱዳን ከሰባት መቶ ኪሎ ሜትር በላይ የሚያዋስኗቸውን የጋራ ድንበርን ይጋራሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም