በጋምቤላ ክልል ከ137 ሺህ ለሚበልጡ ህፃናት የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ነው

86
ጋምቤላ ታህሳስ 15/2011 በጋምቤላ ክልል ከ137 ሺህ ለሚበልጡ ህፃናት የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት በዘመቻ እየተሰጠ መሆኑን የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ አስታወቀ። ለዘመቻው ስኬት ወላጆችና ኅብረተሰቡ ህፃናቱን  በማስከተብ ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቋል። በቢሮው የጤናና ጤና ነክ ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ የስራ ሂደት ባለቤት አቶ ኦኬሎ ቾል ለኢዜአ እንደገለጹት ክትባቱ እየተሰጠ ያለው ጋምቤላ ከተማን ጨምሮ በ13 ወረዳዎችና በስድስት የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ነው። በዲማ ወረዳ ክትባቱ ቀደም ሲል በመሰጠቱ በአሁኑ ዘመቻ አልተካተተም። ለአንድ ሳምንት በሚቆየው ዘመቻ  ከስድስት ወራት እስከ 15 ዓመት ዕድሜ ክልል የሚገኙ ህፃናት ክትባቱን እንደሚወስዱ ተናግረዋል። ክትባቱን መስጠት ያስፈለገው በቅርቡ በወረዳዎችና በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች በ50 ህፃናት ላይ በሽታው በመከሰቱና በበሽታው ከተጠቁት ህፃናት መካከልም የሁለቱ ህይወት በማለፉ ምክንያት ነው ብለዋል። ክትባቱ በየቀበሌው በጊዜያዊነት በተቋቋሙ የክትባት መስጫ ጣቢያዎች፣ በትምህርት ቤቶችና በጤና ተቋማት እየተሰጠ መሆኑንም ነው የገለጹት አቶ ኦኬሎ። በዘመቻው አንድ ሺህ 700 የሚጠጉ ባለሙያዎችና በጎ ፈቃደኞች መሰማራታቸውን ገልጸዋል። በጋምቤላ ከተማ በክትባት ዘመቻው ከተሰማሩ ባለሙያዎች መካከል ወይዘሮ ኛኮት ኮንግ እንደተናገሩት ወላጆች ልጆቻቸውን ለማስከተብ ፍላጎትና ተነሳሽነት እያሳዩ ነው ብለዋል። ኅብረተሰቡም ሆነ ወላጆች  ለክትባት ሥራው መቃናት ድጋፍና ትብብር እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል። በጋምቤላ ከተማ 01 ቀበሌ በክትባት ጣቢያ ያገኘናት ወጣት ማህሌት ጫንያለው ወንድሟን ከበሽታው ለመከላከል ወደ ክትባት ጣቢያው ለማስከተብ መምጣቷን ገልጻለች። ኩፍኝ ህጻናትን ከሚያጠቁ በሽታዎች አንዱ ሲሆን፣በወረርሽኝ መልከ እየተከሰተ ለሞት እንደሚዳርጋቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም