ትውልዱ ለነገ የሚያስፈልገውን የእውቀት ስንቅ ለመያዝ ዛሬ ላይ እርስ በርስ መማማር አለበት - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ

106
አዲስ አበባ ታህሳስ 15/2011 ትውልዱ ለነገ የሚያስፈልገውን የእውቀት ስንቅ ለመያዝ ዛሬ ላይ እርስ በርስ መማማር እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ዛሬ ማለዳ በአምቦ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተገኝተው ለተማሪዎች ንግግር ባደረጉበት ጊዜ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እንደተናገሩት፤ አምቦ የነጻናትና የትግል ማዕከል ናት፤ አሁን የተገኘው ነጻነትም የወጣቶች መስዋዕትነት ውጤት ነው። የተከፈለው መስዋዕትነትም በከንቱ ሳይቀር አሁን ላይ በአገሪቱ የእኩልነትና ነጻነት ጮራ እንዲፈነጥቅ ማስቻሉን ገልጸዋል። ''አሁን ያለንበት ጊዜ  ነጻነታችን በትግል ያገኘንበት ነው'' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ነገን እያሰቡ መዘጋጀት ካልተቻለ ባለንበት ሁኔታ ለረዥም ጊዜያት መቆየት እንደሚያስቸግር ጠቁመዋል። ተማሪዎች ከታሪክ መልካም መልካምን በመማር አገሪቱን በመገንባት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል። ይህ ትውልድ ነገ የሚመጣውን ተረድቶ እርስ በርስ መማማር ከቻለ ከራስ አልፎ ለሌሎች መትረፍ እንችላለን ሲሉም ተማሪዎቹን መክረዋል። ለተማሪዎች ክላሽ መሸከም ለነገ ትርጉም ስለማያመጣ ትኩረታቸው ደብተር እና እስክርቢቶ መያዝ ላይ እንዲሆንም አሳስበዋል። ''ትናንት ነጻነት ስለሚያስፈልገን ክላሽ ተሸክመን ነበር'' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፤ አሁን ላይ  ነጻነት በመስፈኑ ተማሪዎች የሚከፍሉት መስዋዕትነት ሌት ከቀን ማጥናት ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል። በመካከላቸው የማያስፈልጉ ነገሮች እንዳይፈጠሩ መጠንቀቅ እንዳለባቸውም መክረዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም