በምዕራብ ኦሮሚያ የህዝቡን ሰላምና የመንግስትን የእለት ተለት ተግባር በሚያውኩ ኃይሎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው

1714

አዲስ አበባ ታህሳስ 15/2011 በምዕራብ ኦሮሚያ የህዝቡን ሰላምና የመንግስትን የእለት ተለት ተግባር በሚያውኩ ኃይሎች ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

በምእራብ ኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ባለፉት ጥቂት ወራት ብቻ በህገ ወጥ ኃይሎች በተፈፀመ ጥቃት 12 የፖሊስ አባላትን ጨምሮ 41 ንጹሃን ዜጎች ተገድለዋል።

ሌሎች 99 ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሷል፤ የአካል ጉዳት ከደረሰባቸው መካከልም 77ቱ የፖሊስ አባላት መሆናቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ጀነራል ኮሚሽነር አለማየሁ እጅጉ ዛሬ በሰጡት መግለጫ አመልክተዋል።

ይህ ህገ ወጥ ተግባር በተለይ በምዕራብና ቄለም ወለጋ ዞኖች የከፋ መሆኑን የተናገሩት ኮሚሽነር ጀነራሉ፤ ዋነኛ የድርጊቱ ፈፃሚም በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራውና “ሸኔ” የተሰኘው የኦነግ ክንፍ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ኮሚሽነር ጀነራሉ እንዳሉት በወለጋ፣ ኢሉ አባቦራና ቡኖ በደሌና በደቡብ ኦሮሚያ ጉጂ  አካባቢዎች ዘረፋንና የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችን ማባረርን ጨምሮ የህዝቡን ሰላማዊ ኑሮ እና የመንግስትን የእለት ተለት ተግባር የሚያውኩ ድርጊቶች ሲፈፀሙ ቆይተዋል።

ህገ ወጥ ኃይሎቹ ከፖሊስ ጣቢያዎችና ሌሎች የመንግስት ተቋማት ከ2 ሺ በላይ የጦር መሳሪያ እና  ከ3 ሚሊዮን በላይ ጥሬ ገንዘብ መዝረፋቸውን ነው ኮሚሽነር ጀነራሉ የገለፁት።

ችግሩ መኖሩ እየታወቀ ፖሊስ ጉዳዩን በትዕግስት ሲመለከተው እንደነበር የገለጹት ኮሚሽነር አለማየሁ፤ “ለዚህም ምክንያቱ መንግስት ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት በማድረግ ላይ ስለነበረ ነው” ብለዋል።

ሆኖም የጸጥታ ሃይሉ ትዕግስት የህይወት ዋጋ እንዳስከፈለ በመግለጽ ዘውትር ከህዝቡ እየቀረበ ያለውን የህግ የበላይነት የማስከበር ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ ይቻል ዘንድ አሁን ጠንካራ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል።

በመሆኑም መንገድ በመዝጋት፣ የኢኮኖሚና  የመንግስታዊ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴን እንደሁም የህዝቡን ሰላም የሚያውኩ አካላትን በህግ አግባብ እርምጃ ለመውሰድ ትዕዛዝ መተላለፉን ገልጸዋል።

የክልሉ ፖሊሲም ከወትሮ የተለየ ዝግጅት አድርጎ ወደ ስራ መግባቱንም ገልጸዋል።

በእስካሁን ጥረትም ”አባቶርቤ” ወይም “ባለሳምንት” በሚል ስያሜ ሰዎችን ሲያስገድሉና ሲገድሉ የነበሩትን  ጨምሮ የተለያዩ የህገ ወጥ ተግባሩ ተሳታፊዎች በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ይህ ከግብ ደርሶ በአካባቢዎቹ ላይ የህዝቡ ሰላማዊ ኑሮ እንዲረጋገጥም የህዝቡ ተሳትፎና እገዛ እንደሚያስፈልግ ኮሚሽነር አለማየሁ፤ የህዝቡን ትብብር ጠይቀዋል።