ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአምቦ መሰናዶ ትምርት ቤት ተማሪዎች ጋር ተወያዩ

151
አምቦ ታህሳስ 15/2011 የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዛሬ ከአምቦ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጋር ተወያዩ፡፡ በወይይቱ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ተማሪዎች  ተቻችለው ለሀገራቸው ሰላምና አንድነት የበኩላቸውን እንዲወጡ መክረዋል፡፡ " ለነገአችሁ አስቡ፤  ለጠላት ወሬ ቦታ ሳትሰጡ ትምህርታችሁን ተከታተሉ፤ በስንት መስዋእትነት የተገኘውን ሰላም ጠብቁ " ብለዋል፡፡ አምቦ የነጻናትና የትግል ማዕከል ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስሩ አሁን የተገኘው ነጻነትም የወጣቶች መስዋዕትነት ውጤት  መሆኑን ጠቅሰው "የተከፈለው መስዋዕትነትም በከንቱ ሳይቀር አሁን ላይ በሀገሪቱ የእኩልነትና ነጻነት ጮራ እንዲፈነጥቅ አስችሏል "ብለዋል። ከዚህ በኋላ በነጻነት ስም የሚፈሰ ደም መኖር እንደሌለበት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለነጻነት የሚያስፈልገው እስክርብቶና ደብተር ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ተማሪዎች ከታሪክ መልካም መልካሙን በመማር ለሀገሪቱ ግንባታ የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል። ከኢትዮጵያ ተሻግረው በአፍሪካም አንድነት እንዲጎለብት ራዕይ ይዘው መማር እንዳለባቸው የመከሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተማሪዎች የነገ ሀገር ተረካቢዎች በመሆናቸው በመስዋዕትነት  የተገኘው ሰላም እንዳይታወክ  በመጠበቅ እርስ በርሳቸው ተግባብተው አንድነታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸውም መልዕክታቸወን አስተላልፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም