ሠራዊቱ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን የሚያከናውናቸውን ውጤታማ ተግባራት ያጠናክራል

90
ድሬዳዋ ታህሳስ 15/2011 መከላከያ ሠራዊት በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን የሚያከናውናቸውን ውጤታማ ተግባራት እንደሚያጠናክር በአገር መከላከያ ሚኒስቴር የኅብረት መረጃ ዋና መምሪያ ኃላፊ ገለጹ። የሁርሶ የ'ኮንቲጀንት' /ተጠባባቂ/ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በሰላም አስከባሪነት ያሰለጠናቸውን ከ2ሺህ600 በላይ የሠራዊት አባላት አስመርቋል፡፡ ትምህርት ቤቱ  በስድስተኛ ዙር ካሰለጠናቸው ሰላም አስከባሪዎች መካከል 237ቱ ሴቶች ናቸው፡፡ ኃላፊው ሌተናል ጄኔራል ሐሰን ኢብራሂም በዚ ጊዜ ሠራዊቱ ካነገባቸው ሕገ-መንግሥታዊ ተልዕኮዎች አንዱ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ በሆነው የሰላም ማስከበር ግዳጅ መሰማራት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ተልዕኮውን ለማሳካት በተሰማራችባቸው አገሮች ያስመዘገባችው ውጤት የአገሪቱንና የሠራዊቱን ተቀባይነት በዓለም አቀፍ ደረጃ  ማሳደጉንና ተፈላጊነቱን መጨመሩን ገልጸዋል፡፡መልካም ገጽታዋን በማስተዋወቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል። አገሪቱ በአሁኑ ወቅት  በዳርፉር፣ በደቡብ ሱዳን፣ በአብዬና በሶማሊያ በተሰማሩት አባላት ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ግዳጁን እየተወጣ ይገኛል ሲሉም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ ተልዕኮውን ለማጠናከር የተመረቁት አባላት ሕዝባዊ ወገንተኝነትን በመላበስ የሠራዊቱን መልካም ዝናና ውጤታማነት ማስቀጠል እንዳለባቸው ሌተና ጄኔራል ሐሰን አሳስበዋል፡፡ የትምህርት ቤቱ ተወካይ ኮሎኔል ሚልኬሳ ረጋሳ በበኩላቸው ተመራቂዎቹ የተሰጣቸው ተልዕኮ ተኮር ስልጠና ግዳጅን በብቃትና በጥራት መፈፀም እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ወደ ደቡብ ሱዳን፣ዳርፉርና አብዬ የሚጓዙት የሠራዊቱ አባላት ተልዕኮአቸውን በኃላፊነት እንዲያከናውኑ አሳስበዋል፡፡ ከተመራቂዎቹ መካከል ወታደር ታገሰች ቢሻም የተጣለባትን አገራዊ የአምባሳደርነት ሚና በመወጣት የሠራዊቱን ስምና ዝና እንደምታስጠብቅ ተናግራለች፡፡ ሥልጠናው የሰላም ማስከበር ተልዕኮን  በስኬት ለመፈፀም እንደሚያስችል የተናገረችው ደግሞ ወታደር ሰብለ ገሰሰ ናት፡፡ ''እኔም ሆንኩ እህቶቼ የተጣለብንን ኃላፊነት ለመወጣት ተዘጋጅተናል'' ብላለች፡፡ የአሥር አለቃ ዝና በማርቆስ በበኩላቸው ሕዝብና አገር ያስረከበንን አደራ በሥነ-ምግባርና በሕዝባዊነት እንፈጽማለን ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ኡስማን ፣ጄኔራል መኮንኖች፣ ወታደራዊ አታሼዎች ተገኝተዋል፡፡ ኢትዮጵያ  እንደ አውሮፓውያን  አቆጣጠር ከ1951 ጀምሮ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ እየተሳተፈች መሆኗ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም