ኢትዮጵያ በአለም መገናኛ ብዙሃን

93
ባሳለፍነው ሳምንት የሀገራችን መልካም ገፅታ (positive image) የሚያጎሉ ዘገባዎችን የተለያዩ የአለም መገናኛ ብዙሀን በድረ ገፆቻቸው አስነብበዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ የኤክስቼንጅ ዘገባ  አንዱ ነው፡፡

የጀርመን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እና ቢዝነስ ላይ ትልቅ ተስፋ እንዳላቸው ጥናት ማመለከቱን ነው ድረ ገፁ የዘገበው።

የጀርመን ኩባንያዎች በቀጣይ የፈረንጆቹ አመት በኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ መዋዕለ ነዋያቸውን እንደሚያፈሱ ድረ ገፁ አክሎ አስነብቧል። በከፍተኛ ሁኔታ እየተመነደገ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ በርካታ ኩባንያዎች የመሳተፍ ፍላጎት በማሳየት ላይ ይገኛሉ ያለው ድረገጹ ሀገሪቱ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት የተለያዩ ፖሊሲዎችን እና እስትራቴጂዎች ቀይሳ በመንቀሳቀስ ላይ ትገኛለች ሲል መስክሯል።

የጀርመን የንግድ እና ኢንደስትሪ ማህበር የምስራቅ አፍሪካ ልዑካን ቡድን በሀገሪቱ በተሰማሩ 39 የጀርመን ኩባንያዎች ላይ ጥናት ማካሄዱን የጠቆመው ድረገጹ በጥናቱ ውጤት መሰረትም ኩባንያዎቹ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ እና ዕድገት ከፍተኛ ተስፋ እንዳላቸው ድምዳሜ ላይ መደረሱን አስታውቋል።

የጀርመን የንግድ እና ኢንደስትሪ ማህበር የምስራቅ አፍሪካ ሃለፊ የሆኑት Maren Diale-Schellschmidt ጥናቱ ከተደረገባቸው እና በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን ካፈሰሱ ጀርመናውያን መካከል 64 በመቶ የሚሆኑት በኢትዮጵያ ኢንቨስት በማድረጋቸው ደስተኞች መሆናቸውን መግለጻቸው ትልቅ ትርጉም አለው ሲሉ መግለጻቸውን ዘገባው አመላክቷል። ሃላፊዋ በተጨማሪም በኢትዮጵያ የተለያዩ ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመው ዋነኛው ግን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ነው ሲሉ መግለጻቸውን ዘገባው አካቷል። በ2019 የጀርመን በርካታ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋያቸውን በማፍሰስ እንደሚሳተፉ Maren Diale-Schellschmidt መናገራቸውን ድረገጹ አስነብቧል። በሌላ ዜና ከፍተኛ ቁጥር ያለቸው የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በሚገኙ ኢንደስትሪ ፓርኮች ላይ እንዲሳተፉ የኢትዮጵያ ፍላጎት መሆኑ መገለፁን ዥንዋ ዘግቧል። ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያለቸው የቻይና ባለሀብቶች በሀገሪቱ በሚገኙ ኢንደስትሪ ፓርኮች ላይ እንዲሳተፉ ያላት ፍላጎት ከፍተኛ ነው ሲሉ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት ዳዋኖ ከድር መግለጻቸውን ዢንዋ ዘግቧል። ከፍተኛ ባለስልጣኑ የቻይና ፈጣን ዕድገት በማድነቅ በኢትዮጵያ ባለው የማንፋክቸሪንግ ዘርፍ ቻይናውያን ባለሃብቶች እንዲሳተፉ ጥሪ ማቅረባቸውን ዘገባው አስታውቋል። ኢትዮጵያ ባለፉት አስር አመታት ባለሁለት አሃዝ ዕድገት ስታስመዘግብ ነበር ያሉት ባለስልጣኑ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በቻይና ድጋፍ የአፍሪካ የማምረቻ ኢንደስተሪው ዋነኛ መገኛ ለመሆን እየጣረች ትገኛለች ብለዋል። የተባበሩት አረብ ኤምሬት እና ኢትዮጵያ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር መስማማታቸውን  የዘገበው ደግሞ ኤመሬት የዜና ኤጀንሲ ነው። ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸውን ለማጠናከር የተስማሙት የተባበሩት አረብ ኤሜሬትን በመጎብኘት ላይ የሚገኙት የኢፊድሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ከሀገሪቱ የውጭ ጉዳዮች ሚኒስትር ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ ጋር ተገናኝተው በመከሩበት ወቅት መሆኑም ተገልጿል። ሁለቱም ሀገራት በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ግብርና እና አቪየሽን ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር መስማማታቸውን የዜና ኤጀንሲው ዘገባ አመላክቷል። ሁለቱ ሀገራት በበርካታ ዘርፎች የስምምነት ፊርማ ማድረጋቸውን የጠቆመው ዘገባው በተለይም በኤሜሬት የሚሰሩ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ የተፈረመው ፊርማ በቅርቡ ተቋርጦ የነበረውን ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች ወደ ኤሜሬት በማቅናት መስራት እንዲችሉ ያመቻቸ እንደነበር አስታውቋል። ከዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር የጠቅላይ አቃቤ ህግ ሚኒስትሩ ብርሃኑ ጸጋየ እና በኤሜሬትስ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተበጀ በርሄ መገኘታቸውም ተጠቁሟል።

የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ህብረቱ በድረገፁ ላይ ይፋ ባደረገው መረጃ አስታውቋል።

ኢትዮጵያን በመጎብኘት ላይ የሚገኙት የህብረቱ የሰብአዊ ድጋፍ ኮሚሽን ኮሚሽነር ክሪስቶስ ስታይሊንዲስ ህብረቱ በተያዘው ዓመት 89 ዩሮ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል ብለዋል። ኮሚሽነሩ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በህብረቱ የሚደገፉ ፕሮጀክቶችን መጎብኘታቸውን የህብረቱ ድረገጽ ጠቁሟል።

ኮሚሽነር ክሪስቶስ በጉብኝታቸው ወቅት እንደገለጹት ኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ዋነኛ አጋር ናት፤ ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ወሳኝ የሆነ የፖለቲካ ለውጥ በማድረግ ላይ ትገኛለች፤ ህብረቱ እያደረገው ያለው ሰብአዊ ድጋፍ በተፈናቃዮች ለዕለይ ተዕለት ህይወት ላይ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ በአይኔ ተመልክቻለሁ፤ የሰብአዊ መብት እርዳታው እናቶች ልጆቻቸውን እንዲመግቡ ማድረጉን፣ ልጆቻቸው ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ ማስቻሉን እና መድሃኒት በማቅረብ ለጤናቸው አስተዋጽኦ ማድረጉን አይቻለሁ ሲሉ ገልጸዋል።

የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ የሚያደርገው ድጋፍ ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ለጎረቤት ሀገራት ስደተኞችን ለማገዝ እና ድርቅን ለመቋቋም በማለም መሆኑን ድረገጹ አመላክቷል።

በሌላ ዘገባ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በቅርቡ ጂቡቲን እንደሚጎበኙ የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሙሃመድ አሊ የሱፍ ማስታወቃቸውን የቱርክ የዜና አገልግሎት አናዶሉ ዘግቧል። ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸው ሻክሮ ቢቆይም በቅርቡ በኢትዮጵያ አደራዳሪነት በቀጠናው እየታየ ያለውን ትበብር ተከትሎ ግንኙነታቸውን ለማደስ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ዘገባው አመላክቷል። የጉብኝቱ ቀን የተቆረጠ ባይሆንም የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በየሀገራቱ ጉብኝት እንደሚያካሂዱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መግለጻቸውን አናዶሉ በዘገባው አስታውቋል። ሁለቱ መሪዎች መስከረም ወር ላይ ተገናኝተው እንደነበር እና እሳቸውም ከኤርትራ አቻቸው ጋር መገናኘታቸውን ያወሱት ሙሃመድ አሊ የሱፍ በሀገራቱ መከካከል ዕርስ በርስ መተማመንን ማሳደግ እንደሚገባ አስታውቀዋል። ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በቀጠናው ያለውን ትብብር እና ሰላም ለማሳደግ የወሰዱት ሀላፊነት የተሞላበት እንቅሰቃሴ ሀገራቱ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ እና ቀጠናው እንዲረጋጋ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን በመግለጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እውቅና ሊሰጠው ይገባል ማለታቸውን ዘገባው አካቷል። ራድዮ ሸበሌ አምባሳደር ሸምሰዲን አህመድ በሶማሊላንድ የኢትዮጵያ ቆንስላ ሆነው መሾማቸውን በድረገጹ አስነብቧል። አምባሳደር ሸምሰዲን በጂቡቲ እና በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን ማገልገላቸውን ያወሳው ዘገባው ላለፉት አስር አመታት በሶማሊላንድ ቆንስላ ጀነራል በመሆን ያገለገሉት በርሄ ተስፋይ በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ መዛወራቸውን አስታውቋል። ሶማሊላንድ ነጻነቷን ካወጀች ጀምሮ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን ድረገጹ በዘገባው አስታውቋል። ኳታር በዲፕሎማሲ እና ኢኮኖሚ ዘርፎች ከፍተኛ ስኬትን በማስመዝገብ ላይ ትገኛለች ሲሉ በኳታር የኢትዮጵያ አምባሳደር ምንተስኖት ታደሰ መግለጻቸውን ገልፍታይምስ ድረገጽ አስነብቧል። አምባሳደሩ ይሄንን ያሉት የኳታርን ብሔራዊ ቀን አስመልክተው ለኳታር ዜና አገልግሎት በጻፉት መልዕክት መሆኑን ድረገጹ አስታውቋል። የኳታር ስኬት በቀጠናው እና በአለም አቀፍ ደረጃ ነው ሲሉ አምባሳደሩ መመስከራቸውን ዘገባው አካቷል። ኳታር  በቀጠናው እና አለማቀፍ ደረጃ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ጠቃሚ ሚናን ተጫውታለች ያሉት አምባሳደሩ ለህግ ተገዢ የሆነች እና ሰላም የሰፈነባት ኳታር ችግሮችን ለመፍታት ሰላማዊ መንገዶችን መጠቀሟ የሚያስደንቅ አይደለም ሲሉ በደብዳቤያቸው መግለጻቸውን ዘገባው አመላክቷል። ሐምሳ የሚሆኑ የሩዋንዳ አየር ሀይል አባላት ከኢትዮጵያ አየር ሀይል ማሰልጠኛ በአውሮፕላን ጥገና በዲፕሎማ መመረቃቸውን የሩዋንዳው ጋዜጣ ኒውታይምስ በድረገጹ አስታውቋል። ከተመራቂዎቹ መካከል ሰባት የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውንም መረጃው ጠቁሟል። በምረቃው ወቅት የተገኙት የሩዋንዳ አየር ሃይል አዛዥ ሜጀር ጀነራል ቻርለስ ካራምባ የሁለቱ ሀገራትን ግንኙነት ትብብር አድንቀው በተለይ ግን የአየር ሀይሉ ማዘዣ የሩዋንዳው አየር ሀይል አባላትን ስልጠና በመስጠት ማበረታታቱን አወድሰዋል። ስልጠናው የሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ እና ወንድማዊ ግንኙነት ውጤት ነው ማለታቸውንም ዘገባው አካቷል። በመጨረሻም ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነታቸውን ካደሱ ወዲህ 27 ሺ በላይ የሚሆኑ ኤርትራውያን ወደ ኢትዮጵያ በመግባት የስደተኝነት ጥያቄ ማቅረባቸውን ኤኤፍፒ አስታወቀ። የዜና አውታሩ ከአውሮፓ ህብረት ያገኘውን መረጃ ዋቢ በማድረግ እንዳሳታወቀው ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነታቸውን በማደስ ድንበሮቻቸውን ክፍት ካደረጉ ወዲህ ወደ ኢትዮጵያ የሚሰደዱ ኤርትራውያን ቁጥር እጅግ እያሻቀበ እንደሚገኝ አመላክቷል። ከ24ሺ በላይ የሚሆኑት ኤርትራውያን በሰሜን ኢትዮጵያ እንዳባጉና በኩል በመግባት የስደተኝነት ጥያቄ በማቅረብ ፎርም መሙላታቸውን የጠቆመው ዘገባው ቀሪዎቹ ሶስት ሺ አምስት መቶ የሚሆኑት ደግሞ ጥያቄውን ያቀረቡት በአፋር በኩል መሆኑን ገልጿል። በኢትዮጵያ የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ቁጥር እስከ ባለፈው ነሃሴ ወር ድረስ 174ሺ እንደነበር የዜና አውታሩ ዘገባ አውስቷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም