በሀገርህን እወቅ ክበባት የሚዘጋጁ ጉብኝቶች በህዝቦች መካከል መቀራረብን ይፈጥራሉ - መምህራንና ተማሪዎች

280
ታህሳስ 14/2011 በየትምህርት ቤቱ የተቋቋሙ የሀገርህን እወቅ ክበባት በተለያዩ አካባቢ የሚያደርጉት ጉብኝት  ሀገራዊ አንድነትን የማጎልበት ሚና እንዳለው ኢዜአ ያናገርናቸው ተማሪዎችና መምህራን ይገልጻሉ። በትምህርት ቤቱ የሃገርህን እወቅ ክበብ በተዘጋጁ ጉብኝቶች በመሳተፍ  በተለያዩ  አካባቢዎች የሚገኙ ተፈጥሮአዊና ታሪካዊ ቅርሶችን ለመጎብኘት መቻሏ የኢትዮጵያን ታሪክ እንድታውቅ እንደረዳት የተናገረችው በአጼ ፋሲል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ መሰረት ተረፈ ናት  ፡፡ ጉብኝቱም የኢትዮጵያ ታሪክ የብሄር ብሄረሰቦች ጥረት ድምር ውጤት መሆኑን ለመገንዘብ አስችሎኛል በማለትም ትገልጻለች። ሌላኛዋ የአጼ ፋሲል ተማሪ ፋሲካ ደጀኔ “ጉብኝቱ ሀገሬን እንዳውቅ ያግዘኛል፣ሀገሬን ሳውቅ ደግሞ እራሴን አወኩ ማለት ነው፤ ይህም የሀገር ፍቅር ስሜት አሳድሮብኛል” ነው ያለችው፡፡ ተማሪ ፋሲካ እንዳለችው ከሰዎች ከምትሰማው የበለጠ  በጉብኝቱ ስለኢትዮጵያ  እንዲትረዳ አስችሏታል። አንዳአንድ ሰዎች በማህበራዊ ሚዲያ በሚያስተላልፉት የተሳሳተ መረጃ ስለ ሃገራችን የተዛባ አመለካከት ሊኖረን ስለሚችል በተግባር ማየቱ የተሻለ ነው የምትለው ደግሞ  ተማሪ እድላዊት  በጊዜው ናት ፡፡ በዚሁ ትምህርትቤት የማህበራዊ ሳይንስ መምህር ጋሻው የሽጥላ ከ2007 ጀምሮ የክበብ አባል መሆናቸውን ጠቅሰው በየአመቱ በሚዘጋጀው ጉብኝት ተማሪዎች በመዲናዋና የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ታሪካዊና ተፈጥሮአዊ ቅርሶችን መጎብኘታቸውን ይናገራሉ፡፡ ተማሪዎች ስለ ሀገራቸው በቂ እውቀት መጨበጥ ሲችሉ ሀገር ወዳድ ዜጋ መፍጠር ይቻላል ያሉት መምህር ጋሻው ከልጅነታቸው ጀምሮ ስለሀገር ፍቅር ማስተማር ይገባል ብለዋል፡፡ በጉብኝታቸው የተለያዩ የብሄር፣ ብሄረሰበች ባህልና አኗኗር ያላቸውን ግንዛቤ ስለሚያሳድግላቸው ብዝሃነትን ከልጅነታቸው ጀምሮ እንዲለማመመዱ በማድረግ ተቻችሎና ተካብሮ የመኖር ዘዴን እንዲያዳብሩ ያስችላልም ነው ያሉት ፡፡ የኒውኤራ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ግርማነሽ ብረሃኑ በበኩሏ በሙዚሞችና የመስክ  ጉብኝት የኢትዮጵያን ታሪክ፣ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰብ ባህሎችን የሚያንጸባርቁ አልባሳትና ቁሳቁሶችን በማየቷ የኢትዮጵያ ታሪክ የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ድምርውጤት መሆኑን ለመረዳት  መቻሏን ትገልጻለች። በጉብኝቱ  ታሪካችን በቀደምት ዘመናት ቀዳሚ እንደነበርን ያሳያል ያለችው ተማሪ ግርማነሽ    የተለያየ ቋንቋና ሃይማኖት ቢኖረንም ሁላችን በኢትዮጵያዊነታችን የተሳሰርን ነን ብላለች፡፡ ተማሪዎች ከንድፈ ሀሳብ  ትምህርት ባለፈ  ሀገራቸውን በተጨባጭ ሊያውቁ እንደሚገባ ያመለከቱት በኒውኤራ ትምህርት ቤት የክበቡ አስተባባሪ መምህር ዳንኤል አበበ ይህን ማድረግ የሚቻለውም የሀገሪቱን የተለያዩ አካባቢዎችን ማየት ሲችሉ ነው ብለዋል፡፡ የተለያየ ሀይማኖትና ብሄር ያላቸው በአንድ ክፍል የሚማሩ ተማሪዎች በአንድነት በኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ  ለመቅረጽ አመቺ መሆኑን ነው ያሉት መምህሩ የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነትም እንደሚወጡ ገልጸዋል። ከመደበኛው ትምህርት ጎን ለጎን ለተማሪዎች ስለሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ግንዛቤ በመስጠት  ብዥታዎችን ማጥራት አስፈላጊ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ገዛሀኝ አባት በበኩላቸው የሀገርህን እወቅ ጉብኝቶች በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወኑ ሚኒስቴሩ የድጋፋ ደብደቤ ከመጻፍ ጀምሮ  ሌሎች ድጋፎችን እንደሚያድርግ ጠቅሰዋል፡፡ የሀገር ውስጥ ጉብኝት የጋራ እሴቶችን ለማወቅና  የባህል ትስስሩን በማጠናከር በህዝቦች መካከል የአንድነት መንፈስ እንዲጎለብት ያስችላልም ነው ያሉት አቶ ገዛሄኝ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም