በማህበር ለተደራጁ ሴቶች ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ የብድር አገለግሎት ተሰጠ

64
ሆስዕና ታህሳስ 14/2011 በሀድያ ዞን በተለያዩ ማህበራት ለተደራጁ ሴቶች ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር መሰጠቱን የዞኑ ሴቶች ፣ህጻናትና ወጣቶች መምሪያ ገለጸ፡፡ የመምሪያው  ኃላፊ ወይዘሪት ዲላሜ ደመቀ ለኢዜአ እንደተናገሩት የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተለያዩ መስኮች በማደራጀት እንዲሰሩ ድጋፍ እየተደረገ ነው፡፡ በዞኑ በገጠርና በከተማ በማህበር የተደራጁ ሴቶች በእርባታ ፣በአነስተኛ ንግድ ፣በባልትናና ሌሎች መስኮች እንዲደራጁ በተከናወነው ተግባር በ2010/11 በጀት ዓመት 60 ሺህ 446 ሴቶችን ማደራጀት ተችሏል፡፡ እነዚህ ማህበራት 19 ሚሊዮን 175 ሺህ 462 ብር ብድር ተሰጥቷቸው ወደ ስራ እንደገቡ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪ ሴቶች በፖለቲካው መስክ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያሳድጉ በፌዴራል ደረጃ የተተገበረውን የሴቶች አመራርነት መሰረት በማድረግ የግንዛቤ ማሳደጊያ ስልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ በዞኑ አናሌሞ ወረዳ የሊረንሴ ሴቶች የቁጠባ ማህበር አባል ወይዘሮ ብርሀነሽ ካሳ በሰጡት አስተያየት  ተደራጅተው በቆጠቡት ላይ ተጨማሪ ብድር በመውሰድ ሁለት የአህያ ጋሪዎችን በመግዛት ኑሯቸውን ለማሻሻል እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከሚያገኙት ገቢ ትምህርታቸውን በመከታተል በአሁኑ ወቅት በማህበሩ ውስጥ በሂሳብ ሰራተኛነት ተቀጥረው በመስራት ላይ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡ ተደራጅተው በቆጠቡት ገንዘብ ከማህበሩ አባላት ጋር በግ ማድለብ መጀመራቸውን የገለፁት ደግሞ በሆሳዕና ከተማ የሄጦ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ዘነበች ሱልዶሎ ናቸው፡፡ እስካሁን በተደረገላቸው ድጋፍ ኑሮቸውን ለማሻሻል እንዳገዛቸው ተናግረው ወደፊትም ከመንግስት ድጋፍ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ በዞኑ ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ መምሪያ  የልማት እቅድ ባለሙያ አቶ ሊሬ መኮሮ እንዳሉት በዞኑ በተለያዩ ማህበራት ተደራጅተው ወደ ስራ ከገቡ ማህበራት ከ60 ሺህ የሚበልጡት ከሚያገኙት ገቢ  በመቀነስ  59 ሚሊዮን ብር የቆጥባሉ ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም