የቅሬታ ማቅረቢያ ሶፍት ዌር ቴክኖሎጂ ይፋ ተደረገ

1271

ባህርዳር ባህረዳር 14/2011 በአማራ ክልል ” ሄሎ ገቨርንመንት! ይድረስ ለመንግስት” አዲስ የቅሬታ ማቅረቢያ ሶፍት ዌር ቴክኖሎጂ ይፋ ተደረገ።

ቴክኖሎጂው ማንኛውም ሰው ባለበት ቦታ ሆኖ የደረሰበትን በደልና መታረም አለበት ብሎ ያመነበትን ችግር በሞባይልም ሆነ በመደበኛ ስልክ ” 6888″ ደውሎ ማስመዝገብ የሚችልበት ነው።

በሰቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የአፍሪካ መንግስት አስተዳደርና ልማት ተቋም ኃላፊ ዶክተር ብርሃኑ በየነ እንዳሉት ቴክኖሎጂውን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በአማራ ክልል የተተገበረና በቀጣይ ልምድ በመውሰድ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢ ለማስፋት ያለመ ነው።

በዚህም ማንኛውም ዜጋ በሞባይልም ሆነ በመደበኛ ስልክ የሚያቀርበው ቅሬታም ሆነ አቤቱታ ከቀበሌ ጀምሮ ለወረዳ፣ ለዞንና ለክልሉ መንግስት በተመሳሳይ ጊዜ እንዲደርስ የሚያስችልና መድረሱን የሚያረጋግጥ መሆኑን አስረድተዋል።

መንግስት ዜጎችን አዳምጦ ተገቢውን ምላሽ የሚሰጥበት እና ለዜጎች ደግሞ ቅሬታን ለማቅረብ ወደ ወረዳ፣ ዞንና ክልል በመጓጓዝ የሚደርስባቸውን እንግልት ለማስቀረት ፣ ወጪና ጊዜ ለመቆጠብ የጎላ ጠቀሜታ አለው።

መረጃውን በየስራ ዘርፎች በመለየትም በየትኛው የአስተዳደር እርከን መፈታት እንዳለበት የሚያመላክት በመሆኑ ከርዕሰ መስተዳድሩ ጀምሮ ወደ ታች ባለው የስልጣን እርከን ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ እንደሚያግዝ ዶክተር ብርሃኑ አስታውቀዋል።

ከስዊድን የመጡት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያው አቶ ዮናስ ወልደሃይማኖት በበኩላቸው ቴክኖሎጂው በአማራኛ ቋንቋ የሚሰራና ፊደል የቆጠረ አርሶ አደር በቀላሉ እንዲጠቀምበት ተደርጎ የተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለሙያው እንዳሉት ቴክኖሎጂው አቤቱታን፣ ቅሬታንና መስተካከል ያለባቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በጽሁፍ፣ በድምጽና በምስል ለማቅረብ የሚያስችል ከመሆኑም በላይ ማስረጃዎችን አካቶ ለመላክ ያስችላል።

የቅሬታ አቅራቢዎችን ጾታ፣ አካባቢ፣ እድሜ፣ ጉዳያቸውንና ሌሎች መረጃዎችን አካቶ የሚይዝና በተፈለገ ጊዜ አጠቃሎ የሚያወጣ በመሆኑ ለጥናትና ምርምር አጋዝ መሆኑንም አመልክተዋል።

“ቴክኖሎጂው የመንግስት አካላት ለህዝብ ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡ የሚያስችልና ምላሽ የማይሰጡ በቀላሉ ተለይተው እንዲጠየቁ የሚያስችል ነው “ያሉት ደግሞ በአማራ ክልል የቅሬታ ሰሚ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰይዱ እሸቴ ናቸው።

ቴክኖሎጂውን ፈጥኖ በመተግበር አሁን ያለውን ህዝባዊ ለውጥ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስም 6888 የሚል በተለጣፊ/ስቲከር/ የተሰራ በ500ሺህ ኮፒ ተባዝቶ በየቀበሌው በሚገኙ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት እንደሚለጠፍ ተናግረዋል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዳንኤል በላይ ” ቴክኖሎጂው ከቀበሌ ጀምሮ በየደረጃው ለሚገኘው አካላት የቀረቡ አቤቱታዎችን የሚያሳውቅ በመሆኑ የህዝብ የመደመጥና ምላሽ የማግኘት መብትን የሚያረጋግጥ ነው” ብለዋል፡፡

በከተማ አስተዳደራቸው ከይዞታ ማረጋገጫ፣ ከልማት ተነሺዎች የምትክ ቦታና የካሳ ክፍያ፣ ከግብርና ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎች በርካታ መሆናቸው ጠቁመዋል።

አሁን የመጣው ቴክኖሎጂ በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ ቀበሌዎችና መስሪያ ቤቶች የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት ብሎም ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።

የቅሬታ ማቅረቢያ ቴክኖሎጂው ይፋ የሆነው ከወረዳ እስከ ክልል የመጡ አፈ ጉባኤዎች፣ ከንቲባዎች፣ አስተዳዳሪዎችና የቅሬታ ሰሚዎች በተገኙበት የእንጅባራ መድረክ ሲሆን ስለአጠቃቀሙም የግማሽ ቀን ስልጠና ተሰጥቷል።