ለውጡ የዴሞክራሲ ተቋማት የስራ አስፈጻሚ ጣልቃ ገብነት ለማስወገድ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አስችሏል--- ዋና እንባ ጠባቂ

98
ባህርዳር ታህሳስ 14/2011 "በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ የዴሞክራሲ ተቋማት የነበረባቸውን የስራ አስፈጻሚ አካላት ጣልቃ ገብነት ለማስወገድ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አስችሏል" ሲሉ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ ተናገሩ። ከክልል እስከ ወረዳ የሚገኙ አፈ ጉባኤዎች፣ ቅሬታ ሰሚዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት  የተሳተፉበት የውይይት መድረክ በእንጅባራ ከተማ ተካሂዷል። በመድረኩ የተቋሙ ዋና እንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ  እንዳስታወቁት ባለፉት ዓመታት የነበረው የአስፈጻሚ ኣካሉ ጣልቃ ገብነት አሁን ላይ በመጣው ለውጥ ተወግዷል። "ይህም በህግ የተደነገጉ የዜጎች መብቶችና ጥቅሞች በአስፈጻሚ አካሉ ሳይሸራረፉ መተግበራቸውን በመከታተልና በመቆጣጠር ተጠያቂነትን ለማስፈን ያስችላል "ብለዋል። ተቋማቸው በዜጎች ላይ የሚፈጸሙ አስተዳደራዊ በደሎችን በማስወገድና የመገናኛ ብዙሃን የመረጃ ነጻነትን በማሰፈን በሀገሪቱ ልማት ሁሉም ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትኩረት የሚሰራበት ጊዜ ላይ መደረሱን ገልጸዋል። የመድረኩ ተሳታፊዎችም የመንግስት ግልጽነትና ተጠያቂነት ከምንጊዜውም በላይ በማስፈን እየመጣ ያለው ለውጥን ዳር ለማድረስ በቅንጅት በመስራት በየአካባቢያቸው የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ማስወገድ እንዳለባቸው አሳስበዋል። በተቋሙ የባህር ዳር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት እንባ ጠባቂ አቶ ጋሻነው ደሴ በበኩላቸው  ከህዝብ የሚመጡ ጥቆማዎችና በራስ ተነሳሽነት አስተዳደራዊ በደሎችን በመመርመር መፍትሄ እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ በዚህም ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ከ94ሺህ በላይ የሀብረተሰብ ክፍሎች ያቀረቧቸውን ከአስተዳደራዊ በደሎች ጋር የተያያዙ ከ2ሺህ 800 በላይ የአቤቱታ መዝገቦች በመመርመር ምላሽ እንዲያገኙ ሲሰራ መቆየቱን አመልክተዋል። ከእነዚህም አንድ ሺህ 200 መዝገቦች ተቀባይነት አግኝተው በተለያየ ደረጃ መፍትሄ እንዲያገኙ የተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ቀሪ መዝገቦች ከባለጉዳዮቹ ጋር በመወያየት ምላሽ ማግኘታቸውን አስረድተዋል፡፡ አቶ ጋሻው አንዳሉት በተጨማሪም በአስፈጻሚ አካሉ ሲደርስ የነበረውን ጣልቃ ገብነት ለማስወገድ ተከታታይ የሆነ የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረክ ተካሄዷል፤ በዚህም ዜጎች መብታቸውንና ጥቅማቸውን በነጻነት ከሚጠይቁበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። "በሀገራችንም ሆነ በአማራ ክልል የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል የህግ የበላይነት ማስፈን ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው" ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ትልቅሰው ይታያል ናቸው፡፡ አሁን ላይ አስፈጻሚ አካሉን፣ በቁጥጥርና ክትትል ባለድርሻ የሆኑ  በአንድ ላይ ያሳተፈ የግንዛቤ ፈጠራ መካሄዱ ተቀናጅቶ በመስራት ህዝቡ የሚፈለገውን ለውጥ ለማስቀጠል የሚኖረው ሚና የጎላ መሆኑን ተናግረዋል። ከሰሜን ጎንደር ዞን የቅሬታ ሰሚ ባለሙያ ወይዘሮ አዲስ ሙሉጌታ እንደገለጹት  በዞናቸው ከሰሜን ፓርክ የተነሱ  የህብረሰብ ክፍሎች የካሳ ክፍያ፣ በማሀበር ተደራጅተው የመስሪያ ቦታ የሚሰጣቸው ዜጎች የፍትሃዊነት ጥያቄና የአገልግሎት አሰጣጥ ዋና ዋና ችግሮች ናቸው፡፡ ችግሩ እንዳለ ቢታመንም አቤቱታዎችን መርምሮ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ ተፈጻሚነቱ ውሱንነት የነበረው በመሆኑ በመድረኩ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የነበሩባቸውን ክፍተቶች በማየት በቀጣይ በጋራ ለለውጥ እንዲሰሩ ተነሳሽነት እንደሚፈጥር ገልጸዋል። ከታህሳስ 12/2011 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት በተካሄደው የግንዛቤ ፈጠራ መድረክ ከ450 በላይ አፈ ጉባኤዎች፣ ከንቲባዎች፣ አስተዳዳሪዎችና የቅሬታ ሰሚዎች ተሳትፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም