የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማህበራትና ዩኒዬኖች ሚና ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል

119
አዳማ ታህሳስ 13/2011 የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማህበራትና ዩኒዬኖች በፍትሃዊ የፋይናንስ ተደራሽነትና ተጠቃሚነት ሂደት ያላቸውን ሚና ለማሳደግ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ አስታወቀ። በከተሞች ፍትሃዊ የፋይናንስ  ተደራሽነትና ተጠቃሚነትን እውን ለማድረግ ያለመ የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ ተካሂዷል። የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲ ሙሐመድ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ማህበራቱ በከተሞች የድህነት ቅነሳ ፕሮግራም ውስጥ ለድሃው ኅብረተሰብ አነስተኛ ፋይናንስ በማቅረብ ረገድ ድርሻቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው። በዚህም በአገሪቱ የተጀመረውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ በየደረጃው የኅብረተሰቡ ተደራሽና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ያስችላል ብለዋል። በአገሪቱ ባሉት ከ17ሺህ በላይ ማህበራት ዜጎች እንደ አቅማቸው የሚቆጥቡበትና የብድር አገልግሎት እንደሚያገኙም አቶ አብዲ ተናግረዋል። መድረኩ ተቋማቱ ኅብረተሰቡን በፍትሃዊነት እንዲደርሱና ሁሉንም በየደረጃው ተጠቃሚ  ለማድረግ ያለመ ንቅናቄ መሆኑን ገልጸዋል። የአዲስ አበባ ከተማ ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ዓሊ በበኩላቸው በከተማዋ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ህይወት ለመቀየርና ከድህነት ለማውጣት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ማህበራቱ ሚናቸው እየተጫወቱ ናቸው ብለዋል። ባለፈው ዓመት ከሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ብድር በማሰራጨት ከ180 ሺህ በላይ የሚሆኑት ዜጎች በተለያዩ የንግድ ዘርፎች መሰማራታቸውን አስታውቀዋል።በተመሳሳይ ወቅት ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ በቁጠባ መሰብሰቡን ተናግረዋል። ተቋማቱ የልማትና ኢንቨስትመንት ምንጮች እንዲሆኑ አቅማቸውን የማጠናከር፣ የሰው ኃይሉን የማብቃትና የቁጠባ ባህል ማጎልበት ላይ አትኩረው በመሥራት ላይ እንደሚገኙ ኃላፊው ገልጸዋል። የኤጀንሲው የኅብረት ሥራ ማህበራት ልማት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ዱፌራ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ የማህበራቱን አቅም በማጠናከር በአነስተኛ የፋይናንስ ኢንቨስትመንት ልማት ውስጥ መግባት እንዳለባቸው አመልክተዋል። በተቋማቱ ፍትሃዊ የፋይናንስ አቅርቦትና የዜጎች ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የዘርፉን ህጎች፣ዓዋጆችና ደንቦችን በማሻሻል ወደ ተሻለ እድገት እንዲሸጋገሩ ማድረግ ይገባል ብለዋል። በአሁኑ ወቅት ዓዋጅ ቁጥር 985/2009 ተሻሽሎ ቢወጣም፤ ለአፈፃፀምና ለአተገባበሩ የሚያስፈልገውን መመሪያ ማስተካከል ያስፈልጋል ያሉት ጥናት አቅራቢው፣ በአነስተኛ የፋይናንስ ኢንቨስትመንት ውስጥ በመሳተፍ ድህነትን በመቀነስ ሚናቸውን መጫወት እንደሚገባቸው አስረድተዋል። በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ21 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል የሚያንቀሳቅሱ የኅብረት ሥራ ማህበራትና ዩኒየኖች ይገኛሉ። በመድረኩ ላይ በአዲስ አበባ ገንዘብና ቁጠባ ማህበራት የተደራጁ ማህበራትና ዩኒዬኖች ተወካዮችና ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም