በመዲናዋ 129 ቦታዎች በጎዳና ንግድ ለተሰማሩ ነጋዴዎች ተላልፈዋል

72
አዲስ አበባ ታህሳስ 13/2011 የአዲስ አበባን የጎዳና ላይ ንግድ ስርዓት ለማስያዝ 129 ቦታዎች በጎዳና ንግድ ላይ ለተሰማሩ ነጋዴዎች መተላለፋቸው ተገለጸ። የከተማዋ ንግድ ቢሮ እንዳስታወቀው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ7 ሺህ በላይ በጎዳና ንግድ የተሰማሩ ነጋዴዎችን ህጋዊ አድርጓል። በቢሮው የመንገድ ላይ ንግድ ስራ ማስያዝ ዳይሬክተር አቶ ዳኛቸው ሉሌ እንዳሉት በከተማዋ እየተስፋፋ የመጣውን የጎዳና ላይ ንግድ ስርዓት ማስያዝ የሚያስችል ዕቅድ ተቀርጾ በ2010 እና 2011 ዓ.ም የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል። በጎዳና ላይ ንግድ የተሰማሩ ነጋዴዎች በነዋሪነት መታወቂያ፣ በዕድሜና በሌሎች ፈቃድ መስጫ መስፈርቶች ተለይተው ከተመዘገቡት 32 ሺህ 906 ነጋዴዎች መካከል 7 ሺህ 726ቱን ወደ ስራ ማስገባት እንደተቻለ ገልጸዋል። በዚሁ መሰረት በየካ፣ ቦሌና ጉለሌ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ 129 ቦታዎች ለነዚሁ ነጋዴዎች መሰጠታቸውንና ሁለት ዓመት ከተገለገሉበት በኋላም ለሌሎች እንደሚያስተላልፉት ተናግረዋል። የከተማዋን ገጽታ የሚያበላሹ ነገሮች በዳሰሳ ጥናት ተለይተው መፍትሄ እየተሰጣቸው ቢሆንም በተለይ ህፃናት በጎዳናዎች ላይ የሚያስቀምጡት የክብደት መመዘኛ ለስራቸው እንቅፋት እየሆነ መምጣቱን አቶ ዳኛቸው ጠቁመዋል። በመገናኛ፣ ፒያሳ፣ አውቶቡስ ተራና ሌሎች አካባቢዎች ዕድሜያቸው ለስራ ያልደረሱ ህፃናት በዚህ ስራ ተሰማርተው እንደሚታዩም ነው ያስረዱት። ይህም የመዲናዋን ገፅታ የሚያበላሽ በመሆኑ መገናኛ ብዙሃን ዕድሜያቸው ለስራ ያልደረሱ ህፃናትን ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚያሰማሩ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ እንዲሰሩ አመልክተዋል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም