በኢትዮጵያ ተመሳሳይ መርህ ያላቸው ፓርቲዎች በጥምረት የሚሰሩበት ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው-ፓርቲዎች

91
አዲስ አበባታህሳስ 13/2011 በኢትዮጵያ ተመሳሳይ መርህ ያላቸው ተፎካካሪ ፓርቲዎች በጋራ መስራት የሚያስችላቸው ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች አመለከቱ። ቀደም ሲል በፓርቲዎች መካከል እርስ በርስ ያለመተዋወቅ እንዲሁም የመተማመንና በትብብር የመስራት ስሜት እንዳልነበርም ተነግሯል። ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ አገር አቀፍና ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የተለያዩ ፓርቲዎች በጋራ የሚሰሩበት አጋጣሚ መፈጠሩን ነው የተናገሩት። በ1983 ዓ.ም የተመሰረተው የከንባታ ህዝቦች ኮንግረስ ክልላዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ኤርጫፎ ኤርድሎ እንደሚሉት፤ ፓርቲው አገራዊ ስሜትንና በትብብር መስራትን ዋና ዓላማ አድርጎ የተመሰረተ ነው። ፓርቲው ክልላዊና የከንባታ ዞንን ብቻ ወክሎ የሚወዳደር ቢሆንም በ1993 እና በ1997 ዓ.ም በተካሄዱ አገር አቀፍ ምርጫዎች በዞን ደረጃ ሙሉ ለሙሉ በማሸነፍ የክልሉንና የፌዴራል ፓርላማውን ወንበር መያዝ መቻሉንም ይገልጻሉ። ፓርቲው ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በመስራት የተሻለ ጥንካሬ እንዲኖረው ለማድረግ ለተለያዩ ፓርቲዎች ጥያቄ ቢያቀርብም በፓርቲዎች በኩል አዎታዊ ምላሽ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል። የአረና ትግራይ አመራር አባል አቶ አብርሃ ደስታና የኢትዮጵያ አገር አቀፍ ንቅናቄ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ቀደም ሲል በአገሪቷ ያሉ ፓርቲዎች በመካከላቸው ያለመተማመንና ያለመተባበር ስሜት በመኖሩ በጋራ ለመስራት የነበራቸው ፍላጎት ዝቅተኛ እንደነበር አንስተዋል። በአገሪቷ ከ70 በላይ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ አብዛኞቹ ፓርቲዎች ተመሳሳይ ዓላማና መርህ ያላቸው ቢሆንም ውህደት በመፍጠር በጋራ ሲሰሩ አይስተዋልም። አስተያየት ሰጪዎቹ እንደሚሉትም ቀደም ሲል የነበረው የአገሪቷ ፖለቲካዊ ሁኔታ በፓርቲዎቹ መካከል መለያየትን የሚፈጥር እንጂ ወደ አንድነት የሚያመጣ አልነበረም። የፓርቲዎቹ ህውደት መፍጠር ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲ ከመፍጠር ባለፈ ህዝቡም የሚመርጠውን ዕጩ በአግባቡ እንዲረዳ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር ሚሊዮን ቱማቶ በበኩላቸው ''እንደ ፓርቲ በቁጥር አነስተኛ የሆኑ ፓርቲዎች ኖረው ከገዥው ፓርቲ ጋር ሰላማዊ፣ ነጻ፣ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ህጋዊና ህዝባዊ ምርጫ እንዲኖር ለሚደረገው ጥረት በጋራ ለመስራት ፍላጎቱ አለ፤ የመሰባሰቡም ሁኔታ ጥሩ ነው'' ብለዋል፡፡ ''ፓርቲዎች ወደ አንድ ቢቀራረቡ አንድ ሀሳባቸውን መግለጽ ይችላሉ መግባባት ይችላሉ አሁን በጣም የተለያየ ነው መግባባት ስለሌለ ነው ወይም ደግሞ መነጋገር ዕድሉ የለንም ለመነጋገርም አብዛኛዎቻችን ልዩነት የለንም ስለዚህ ባለመገናኘታችን በየሰፈራችን ዝም ብለን እየተደራጀን ስለመጣን ነው'' በማለት የገለጹት  የአረና ትግራይ አመራር አባል አቶ አብርሃ ደስታ ናቸው፡፡  የመላ ኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ኑር ሙደሲር በበኩላቸው ''የክልል ፓርቲዎችም ሆነ አገር አቀፍ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ አንድነትና በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ጉዳይ የማይደራደሩ ከሆነ ከማንኛውም ፓርቲ ጋር ተገናኝቶ ይሰራል ፤ወደፊትም ለመስራት የተለያዩ ድርድሮች ላይ ነው ያለነው'' ብለዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚከተሉት መርህ መሰረት በጥምረት ቢሰሩ መንግስት ድጋፍ ለማድረግ የሚያመቸው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መናገራቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም