በምዕራብ ሸዋ በ354 ሺህ ሄክታር በላይ ሰብል በዘመቻ ተሰበሰበ

63
አምቦ ታህሳስ 13/2011 በምዕራብ ሸዋ ዞን ከ354 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ ላይ የደረሰ ሰብል በዘመቻ መሰብሰቡን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። በዞኑ የሚገኙ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ለአንድ ሳምንት በሰብል ስብሰባው መሳተፋቸው ተገልጿል። የጽህፈት ቤቱ የአዝእርት ልማት ባለሙያ አቶ ተስፋዬ ድሪርሳ ለኢትዮጵያ ዜና አገልገሎት እንደተናገሩት ሰብሉ የተሰበሰበው በመኸር ወቅት ታርሶ በዘር ከተሸፈነው 615 ሺህ ሄክታር ማሳ ውስጥ ነው። "ሰብሉ በዘመቻ በመሰብሰቡ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ይደርስ የነበረውን የምርት ብክነት ለመታደግ ተችሏል" ብለዋል። አርሶ አደሩ በተናጠልና በቡድን በመሆን ሰብልን እየሰበሰበ መሆኑን ተናግረዋል። የአምቦ ወረዳ  ነዋሪ አርሶአደር በዳሶ በንቲ በሰጡት አስተያየት ተማሪዎች ባደረጉላቸው እገዛ ከአንድ ሄክታር ተኩል ማሳቸው ላይ የደረሰ የጤፍና የስንዴ ሰብላቸውን አጭደው ከምረዋል። ''ከግብርና ባለሙያዎች የተሰጠኝን ምክር በመጠቀም የደረሰ ሰብል ከብክነት በፀዳ መልኩ ሰብሰቤ ጨርሻለሁ"ያሉት ደግሞ የወረዳው ነዋሪ አርሶ አደር መርጋ አበበ ናቸው፡፡ የዳኖ ወረዳ ነዋሪ አርሶአደር ለሜሳ ቡልቲ በበኩላቸው "ተማሪዎች ባደረጉልኝ እገዛ ከግማሽ ሄክታር ማሳ ላይ የደረሰ የስንዴ ሰብል በቀላሉ አጭጄ መከመር ችያለሁ" ብለዋል። የተማሪዎቹ ድጋፍ ከዚህ ቀደም ለምርት ስብሰባ ያባክኑት የነበረውን ጊዜና ጉልበት እንደቀነሰላቸው የገለጹት አርሶ አደር ለሜሳ ሰብሉ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ሳይጎዳ መሰብሰቡን ተናግረዋል። የአምቦ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪ ሊኪሳ ፊጡማ እንዳለው ከሚማርበት አምቦ ከተማ ወደ ባኮ በመሄድ በወላጆቹንና በጎረቤቶች ማሳ ላይ የነበረን የደረሰ የጤፍና የሰንዴ  ሰብል አጭዶ በመከመር መሳተፉን ተናግሯል። ከቤተሰቦቼ ማሳ ላይ የነበረ የደረሰ ሰብል በዝናብ ሳይጎዳ በወቅቱ በመሰብሰቡ በበጋው ወራት አምቦ ቁጭ ብየ የሚበቃኝን ቀለብ ሳልሳቀቅ ለመጠየቅ ያስችለኛል ሲል በሰብል ስበሰባው በመሳተፉ የፈጠረበትን ደስታ ገልጿል። የግንደበረት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ አቶምሳ ኃይሉ በበኩሉ ትምህርት ቤቱ ለምርት ስብሰባው በመዘጋቱ ቤተሰቦቹንና አቅመ ደካማ ጎረቤቶቹን ለማገዝ አስችሎኛል ብሏል። በዞኑ እየተሰበሰበ ካለው የመኸር ሰብል ከ19 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም