በአገሪቱ የሕግ የበላይነትና ሰላምን በማረጋገጥ ድርሻቸውን እንደሚወጡ የጅማ ከተማ ነዋሪዎች አረጋገጡ

52
ጅማ ታህሳስ 13/2011 በአገሪቱ የህግ የበላይነትና ሰላምን የማረጋገጥ ተግባራት እንዲጠናከሩ ሚናቸውን እንደሚወጡ በጅማ ከተማ ኅብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ። ነዋሪዎቹ በህግ የበላይነትና በሰላም ግንባታ ዙሪያ ዛሬ ተወያይተዋል። ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ረሻድ አባቡልጉ እንደገለጹት መንግሥት የህግ የበላይነትንና ሰላምን በማጠናከር ለውጡን ለማስቀጠል አቅጣጫ መያዝ ተገቢ ነው። የተያዘው አገራዊ አቅጣጫ ስኬታማ እንዲሆን የበኩላቸውን ደርሻ እንደሚወጡም አስታውቀዋል። የከተማው የሐይማኖት አባት ሐጂ ኑሩ አወል በበኩላቸው "የአሮሞ ህዝብ ሲያነሳቸው የነበሩ ጥያቄዎች እየተመለሱለት ነው" ብለዋል። "የብሄሩ ተወላጆች ከሌሎች ህዝቦች ጋር ተፋቅረውና በአንድነት ተደምረው የመኖር ታሪካቸውን፣ ባህላቸውንና፣ፍልስፍናቸውን ተግባራዊ እያደረጉ ይገኛል" ሲሉም ተናግረዋል። "የከተማው ነዋሪ በአካባቢውም ሆነ በአገሪቱ ሰላምና የህግ የበላይነትን ለማጠናከር በአንድነት ሊሰራ ይገባል" ያሉት ሐጂ ኑሩ፣ እርሳቸውም የሚጠበቅበቅበኝን  እየተወጣሁ ነው  ብለዋል። "መንግሥት የኦሮሞን ህዝብ ጥያቄ ለመመለስም ሆነ  የብሄር/ብሄረሰቦችን መብት ለማስከበር እየወሰደ ያለው እርምጃ የሚበረታታ ነው " ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ሙሀቡባ አባሱልጣን ናቸው ። "በአንጻሩ መንግሥት ሰላምንና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ አቅቶታል በሚል ቅስቀሳ በማድረግ የከተማውንና የህዝቡን ሰላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ አካላት ያሉ በመሆኑ ልንታገላቸው ይገባል" ብለዋል። ህገ-ወጦችን በመከላከል የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ለማስቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ መኪዩ መሐመድ "የአሮሞ ህዝብ ትግል ከየት ወዴት?" በሚል ርዕስ የተዘጋጀ የመወያያ ፅሁፍ ለተሳታፊዎች አቅርበዋል። ከንቲባው በፅሁፋቸው እንዳመለከቱት የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር በመሆን የሰብዊ መብት እንዲከበር፣ፍትሃዊ የስልጣንና የሃብት ክፍፍል እንዲረጋገጥ፣ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፣ የጾታ እኩልነት እንዲከበር ጥያቄ ማቅረቡንም አስታውሰዋል። የፆታ እኩልነት እንዲከበር፣ በኃይማኖቶች መካከል መከፋፈል እንዲቀር፣ ወጣቱ የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆንና ከሌሎች ብሄር/ብሄረሰቦች ጋር በፍቅርና በአንድነት መኖር ካነሳቸው ጥያቄዎች መሆናቸውንም ጠቁመዋል። "ሕዝቡ ያነሷቸው ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ  ምላሽ እየተሰጣቸው ነው" ያሉት ከንቲባው ፣ሌሎች ጥያቄዎች በመመለስ  ሂደት ላይ እንደሚገኙም  ገልጸዋል፡፡ ተከፋፍለው የነበሩ ኃይማኖቶች አንድ እንዲሆኑ መደረጉን፣ ሴቶች ከፍተኛ የፖለቲካ ስልጣን መያዛቸውን፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዳይፈጸሙ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ከንቲባው ለአብነት ጠቅሰዋል። የከተማው ነዋሪዎች መንግሥት የህግ የበላይነትና ሰላምን ለማጠናከር የጀመራቸውን ጥረቶች ለማገዝ የጀመሩትን ተሳትፎ አጠናክረው እንዲያጠናክሩ ከንቲባው ጠይቀዋል። በውይይቱ ከአባገዳዎች፣ ከሐይማኖት አባቶች፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከታዋቂ ግለሰቦች፣ ከባለሃብቶች፣ከሴቶችና ወጣቶች የተውጣጡ 350 የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም