መገናኛ ብዙኃን የህዝብ ድምጽ ሊሆኑ ይገባል…ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል

1839

መቀለ ታህሳስስ 13/2011 መገናኛ ብዙሃን ነጻ አስተሳሰብ የሚራመድባቸው የህዝብ አገልጋይ መሆን እንዳለባቸው የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ተናገሩ፡፡

ላለፉት አራት ወራት በሙከራ ስርጭት የነበረውን የድምጽ ወያነ ትግራይ ቴሌቪዥን ዛሬ ተመርቆ ሥራውን በይፋ ጀምሯል፡፡

በምረቃው መርሐ ግብር ላይ ዶክተር ደብረጽዮን እንዳሉት ’’ድምጽ ወያነ ትግራይ ሬድዮ’’ ከትግል ወቅት ጀምሮ የህዝብ ድምጽ በመሆን የሰራው ታሪክ ሁሌም የሚታወስ ነው።

የትግራይ ህዝብ ሁሌም ለሰላም ፍትሕና እኩልነት የቆመ ሕዝብ በመሆኑ ሃሳቡንና ስሜቱን የሚገልጽበት የመገናኛ ብዙኃን አማራጭ ያስፈልገዋ ብለዋል፡፡

መገናኛ ብዙኃን የሕዝብ ቅሬታዎችንና ችግሮች በመመርመር የመፍትሔ አቅጣጫዎች የሚያስቀምጡ መሆን እንዳለባቸውም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል።

ሬዲዮው ላለፉት 39 ዓመታት በሰላም ልማትና ዴሞክራሲ ግንባታ የተጫወተው አስተዋጽኦ በቴሌቪዥን ስርጭት በመታገዝ የሕዝቡን አስተሳሰብና የልማት ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል፡፡

መገናኛ ብዙኃን በክልሉ የሚካሄደውን የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን በማቀላጠፍ ግዴታቸው እንዲወጡም ጠይቀዋል።

የድምፀ ወያነ  ሬዲዮና ቴሌቪዥን  ዋና ሥራ አስከያጅ አቶ አበበ አስገዶም በበኩላቸው ተቋሙ ራሱን  በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በሰው ኃይል በማደራጀት ሕዝቡን ለማገልገል እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

“የቴለቭዥን ስርጭቱ ሕዝቡ በመልካም አስተዳደርና በዴሞክራሲ ጉዳዮች ግንባታ በቀጥታ የሚሳተፉበት ይሆናል”ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ ለክልልና ለአገር የጋራ ብልጽግናና አንድነት እንዲሁም ህዝቦችን ለማቀራረብ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

በምረቃው ከታደሙት  የመቀለ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ተስፋአለም ዓፋር እንዳሉት የድምጽ ወያነ ትግራይን  የቴሌቪዥን ስርጭት መጀመሩ በጉጉት ሲጠብቀው እንደነበረ ተናግረዋል፡፡

ስርጭቱ በአገሪቱ ሰላም፣ አብሮነትና አንድነት የሚሰራ እንደሚሆንም ተስፋቸውን ገልጸዋል።

በትጥቅ ትግሉ ወቅት በድምጽ ወያነ ራድዮ በጋዜጠኝነት ያገለገሉት ወይዘሮ ሐመልማል ተክለሃይማኖት በበኩላቸው የድምጽ ወያነ ትግራይ ቴሌቪዥንም ለትግራይና ለኢትዮጵያ ህዝቦች የተሻለ አማራጭ ይዞ መቅረብ እንዳለበት ጠቁመዋል።