በጉጂ ዞን ለ642 ማህበራት የ53 ሚሊዮን ብር የገበያ ትስስር ተፈጠረ

65
ነገሌ ታህሳስ 13/2011 የምርትና አገልግሎት ተረካቢ መኖር ሰርቶ ለመለወጥ ተስፋ እንደሚሰጥ የአዶላ ከተማ የገበያ ትስስር ተጠቃሚ ወጣቶች ገለጹ፡፡ በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በአምስት ወራት ብቻ ለ642 አነስተኛና ጥቃቅን ማህበራት የ53 ሚሊዮን ብር የገበያ ትስስር መፈጠሩ ተገልጿል፡፡ በአዶላ ከተማ የ01 ቀበሌ ነዋሪ ወጣት እንዳልካቸው ቦጋለ ከመቱ ዩኒቨርሲቲ በምህንድስና ሙያ ተመርቆ ከሰባት ባልደረቦቹ ጋር በአነስተኛ ጥቃቅን ተደራጅቶ ስራ መጀመሩን ገልጿል፡፡ በአዶላና ሻኪሶ ከተሞች የውስጥ ለውስጥ መንገድ ለመስራት ባለፈው ሐምሌ ወር የ5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የኮብልስቶን ድንጋይ ንጣፍ ስምምነት መፈረማቸውን ጠቁሟል፡፡ በሙያችን አገልግሎት እንድንሰጥ የሥራ ዕድል መመቻቸቱ በአገራችን ሰርቶ ለመለወጥና ሌሎች ወጣቶችንም ለሥራ ያነሳሳል ብሏል፡፡ የዚሁ ከተማ 02 ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ያሬድ ግርማ ከዓመት በፊት ከ10 ባልደረቦቹ ጋር በእንጨትና ብረታብረት ሥራ ቢደራጁም፤ ምርታቸውን  ተረካቢ በማጣታቸው አባላቱ መበተናቸውን ያስታውሳል፡፡ ባለፉት አምስት ወራት ከትምህርት ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ጋር በተመቻቸላቸው የ195 ሺህ ብር የገበያ ትስስር ተሰባስበው ሥራ መጀመራቸውን ገልጿል፡፡ የምርትና አገልግሎት ተረካቢ ካለ፤ ሰርቶ ለመክበርና ለመለወጥ እንደሚቻል ከሥራችን መመልከት ይቻላል ብሏል፡፡ ወጣቱና ባልደረቦቹ የተመቻቸውን የገበያ ትስስር በመጠቀም ለሦስት ትምህርት ቤቶች ከ400 በላይ ጠረጴዛዎችና ወንበሮች ሰርተው አስረክበዋል፡፡ በምህንድስና ተመርቆ ሥራ በማፈላለግ ዓመታትን ያሳለፈው ወጣት አብዲሳ ካቢቴን ከ10 ባልደረቦቹ ጋር ግንባታ ለማካሄድ የ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የገበያ ትስስር እንደተፈጠረላቸው ጠቁሟል፡፡ የገበያ ትስስሩ የተፈጠረው ማህበራት ከማህበራት ከሴክተር መሥሪያ ቤቶች ከባለሀብቶችና ከተጠቃሚ ሕዝብ ጋር እንደሆነ የጉጂ ዞን የሥራ ዕድል ፈጠራና የከተሞች ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ገልጿል፡፡ ትስስሩ በዞኑ 14 ወረዳዎችና በሦስት ከተሞች የሚሰሩ 4 ሺህ 456 ወጣቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን በጽህፈት ቤቱ የገበያ ትስስር አስተባባሪ አቶ ሐብታሙ ግርማ አስታውቀዋል፡፡ የገበያ ትስስር የተፈጠረላቸው ማህበራትም ለደንበኞቻቸው ምርትና አገልግሎታቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብና አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡ ማህበራቱ ምርትና አገልግሎታቸውን በመስጠትና በማቅረብ ላይ ላሉት ለነዚሁ ማህበራት 555 ሄክታር መሬትና 41 የመሸጫ ሱቅ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ የገበያ ትስስሩ ተጠቃሚዎች በግንባታ፣ በኢንዱስትሪ፣ በከተማ ግብርና በርባታ፣ በማዕድን፣ በንግድና በማህበራዊ አገልግሎት ሰባት ዋና ዋና የሥራ ዘርፎች መደራጀታቸውን አስታውቀዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም