የራያ ቢራ ፋብሪካው በ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ወጪ ያስገነባው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ለአገልግሎት በቃ

1481

ማይጨው ታህሳስ 13/2011 የራያ ቢራ ፋብሪካ በአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ወጪ በደቡባዊ ዞን ያስገነባው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ትናንት ተመረቀ።

በምረቃው ስነ ስርዓቱ ላይ የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ አቶ ተወልደ አስፋው እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ የተገነባው በእንዳመሆኒ ወረዳ ማይ ሙቅ በተባለ የገጠር አካባቢ ነው።

ፕሮጀክቱ ግንባታ 500 ሜትር ኪዩብ ውሃ የሚይዝ የውሃ ማጠራቀሚያ ጋን፣ የገላ መታጠቢያ ክፍሎች፣የልብስ ማጠቢያና የእንስሳት ውሃ ማጠጫ ገንዳዎች ግንባታ ያካተተ ነው።

ፋብሪካው ፕሮጀክቱ የገነባው በአካባቢው የሚኖሩ ከ2 ሺህ  በላይ አርሶአደሮች የመጠጥ ውሃ ችግር ለማስወገድ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል።

”እኛ ለቢራ መጥመቂያ ውሃ ከአካባቢው እያገኘን ሕዝቡ በውሃ ችግር መጎዳት የለበትም” ያሉት አቶ ተወልደ፣ ”ፕሮጀክቱን ገንብተን በማበርከታችን ደስታ ተሰምቶናል”  ሲሉም ተናግረዋል።

ፋብሪካው በክልሉ የሚገኙ 800 ችግረኛ ሴት ተማሪዎችን በየዓመቱ 2ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በመስጠት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማድረጉን አቶ ተወልደ ገልጸዋል።

ከ2 ዓመታት በፊት በደቡባዊ ዞን በደረሰው ድርቅ የመኖ እጥረት ያጋጠማቸውን እንስሳት ለመታደግ 22 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የቢራ ተረፈ ምርት መለገሱንም አስታውሰዋል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የውሃ ፕሮጀክቱን ቁልፍ የተረከቡት የመኻን ቀበሌ ሊቀመንበር አርሶአደር ዳርጌ ሃፍቱ እንዳሉት ፕሮጀክቱ አርሶአደሩ ንፅሕናው ያልተጠበቀ የወንዝ ውሃን ለመጠጥነት ሲጠቀም ከቆየበት ሁኔታ ስላወጣው  የተሰማቸውን ደስታገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ የእንስሳት መጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረትም በማቃለሉ መደሰታቸውን የገለጡት ደግሞ ሌላው የቀበሌው ነዋሪ አርሶአደር ኃይለኪሮስ ደስታ ናቸው።

አካባቢው ከርሰ ምድር ውሃ ሃብት ለመስኖ  ልማት በማዋል ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ እንዲፈጥርላቸው አርሶአደር ኃይለኪሮስ ጠይቀዋል።

ለረጅም ጊዜ የወንዝ ውሃን ከእንስሳት ጋር ለመጠጥነት ሲጠቀሙ  በበሽታ እየተጠቃ ሲቸገሩ እንደነበር የሚናገሩት ደግሞ ሌላው አርሶአደር ይርጋ ሐጎስ ናቸው።

አሁን ንፁሕ መጠጥ ውሃ በማግኘታቸው ያጋጥማቸው የነበረውን የጤና ችግር ያስቀራል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ራያ ቢራ ከአምስት ዓመታት በፊት በ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ወጪ በማይጨው ከተማ የተቋቋመና በአሁኑ ጊዜ ከ600 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠሩ ተገልጿል።