በምዕራብ ሸዋ ዞን 208 ነጥብ10 ሚሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሃብቶች ፈቃድ ተሰጠ

86
አምቦ ታህሳስ 13/2011 በምዕራብ ሸዋ ዞን ባለፉት አምስት ወራት 208 ነጥብ 10 ሚሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሃብቶች ፈቃድ መስጠቱን የዞኑ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ገለጸ። ባለሀብቶቹ በተሰማሩባቸው የልማት መስኮች 939 ነዋሪዎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል አግኝተዋል፡፡ በጽህፈት ቤቱ የኢንቨስትመት ቅበላና አማራጭ ዕድሎች ጥናት ዋና የሥራ ሂደት መሪ አቶ ባይሳ ቱፋ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት፣ ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ እስካሁን ለ10 የአገር ውስጥ  ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል። ባለሀብቶቹ በዘመናዊ ግብርና፣ በማእድን፣ በኢንዱስትሪ የሥራ መስኮች ለመሰማራት የሚያስችላቸውን 179 ነጥብ 2 ሄክታር መሬት ተረክበው ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቅሰዋል ። ባለሀብቶቹ በተሰማሩባቸው የልማት መስኮች 939 ለሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ አቶ ባይሳ አመልክተዋል ። እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ ጽህፈት ቤቱ በዞኑ ያሉትን የኢንቨስትመንት አማራጮች ለማስተዋወቅ እያደረገ ባለው ጥረት በዘርፉ የመዋዕለንዋይ ፍሰቱ እያደገ መጥቷል። ባለፈው ዓመት ብቻ በዞኑ 178 ነጥብ 66 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች በዘመናዊ  ግብርና ልማት በመሰማራት ለ199 ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል። በዞኑ ባለፉት ዓመታት በኢንቨስትመንት መስክ የተሰማሩ ባለሀብቶች ወደ ምርት ከመሸጋገራቸው ባለፈ የአካባቢውን ኅብረተሰብ በማህበራዊ አገልገሎቶች እየደገፉ ይገኛሉ። በተጨማሪም የሚያመርቷቸውን የግብርና ውጤቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ በማቅረብ የአካባቢውን ሕብረተሰብ ተጠቃሚ እያደረጉ መሆናቸውን ኃላፊው ገልጸዋል። በምዕራብ ሸዋ ዞን ባለፉት አመታት ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 42 ባለሃብቶች በዞኑ መሬት ተረክበው ወደ ሥራ መግባታቸውን ያስታወሱት አቶ ባይሳ፣ በዚህም ከ5 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን አስረድተዋል። በዞኑ ከሚገኙ ባለሃብቶች መካከል አቶ ብሩክ አዱኛ በሰጡት አስተያየት በቶኬ-ኩታዬ ወረዳ አንድ ሄክታር ቦታ ላይ ባቋቋሙት የታሸገ ውሃ ማምረቻ ለ60 ሰዎች የሥራ እድል ተፈጥሯል። በአምቦ ከተማ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ የሆነው ወጣት ኢዮብ አበበ በበኩሉ በከተማው ባለሀብቶች በሚያካሂዱት የግንባታ ሥራ በመቀጠር በቀን ከ400 ብር በላይ ገቢ በማግኘቱ ተጠቃሚ መሆኑን ገልጿል ። ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ተስፋዬ ዓለሙ እንደገለፁት ባለፉት ዓመታት ባለሃብቶች በከፈቱት የሥራ እድል ተጠቃሚ በመሆናቸው ከሚያገኙት ገቢ በ80 ሺህ ብር የራሳቸው የሆነ መኖሪያ ቤት መስራት ችለዋል። በምእራብ ሸዋ ዞን በዘመናዊ ግብርና፣ በማእድን፣ በኢንዱስትሪ፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በጤናና በቱሪዝም የስራ ዘርፎች ለመሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች 2ሺህ 788 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም