ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ስራውን በኢትዮጵያ ማስፋፋት የሚፈልገውን 'ዳል ዲያሪ ፋርም' ጎበኙ

129
ካርቱም ታህሳስ 12/2011 በሱዳን ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ስራውን በኢትዮጵያ ማስፋፋት የሚፈልገውን 'ዳል ዲያሪ ፋርም' የተሰኘ በእንስሳት ተዋጽኦና በመኖ ልማት ላይ የሚሰራ ኩባንያን ጎበኙ። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሱዳን ያካሄዱት የሶስት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ስኬታማ እንደነበር ተገልጿል። ኩባንያው በኢትዮጵያ ያለው የአየር ሁኔታ ለሚያከናውነው ስራ ምቹ በመሆኑ የእርሻ ስራውን በኢትዮጵያ ለማስፋፋት ጥረት እያደረገ እንደሆነ ገልጿል። የኩባንያው ዋና ስራ አስኪያጅ ኡስማን ዳውደ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ድርጅታቸው በኢትዮጵያ ያለውን የወተት ፍላጎት ለማርካት የሚያስችል አቅምና ተሞክሮ አለው። የእንስሳት ተዋጽኦ ምርታቸውን በአገሪቱ በሚገኙ የንግድ ማዕከላት በማቅረብ ተወዳዳሪ የሆነ ምርት ይዘው ለመቅረብ ፍላጎታቸው ከፍተኛ ነው። ኩባኒያው የተቀናጀ የወተት፣ የእንስሳትና መኖ ማምረቻና መቀነባበሪያ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በሱዳን ውስጥ ብቻ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ካፒታል እንደሚያንቀሳቅስ መረጃዎች ያመለክታሉ። በዘመናዊ መልክ የሚያረባቸው የወተት ላሞችም በወር እስከ 5 ሺህ ሊትር ወተት ያመርታል። በመኖ ምርት ልምድም የላቀ ልምድ ያካበተ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 800 ሄክታር ላይ የሚያመርተውን መኖ ወደ ውጭ እስከመላክ ደርሷል። ከልዑኩ ጉብኝት መልስ አስተያየት የሰጡን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ በበኩላቸው የኩባንያው ከኢትዮጵያ ጋር ቅርበት ያለውና ቀጣናዊ ትስስሩን በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር ፍላጎት ያለው መሆኑን ገልጸዋል። ኩባንያው በኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ከፍቶ ለመስራት ፍላጎቱ ቢኖረውም በተለያየ ማነቆ የተነሳ ሊከፍት ሳይችል መቆየቱን ጠቁመዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ጉብኝት ኩባንያው በኢትዮጵያ ቅርንጫፍ መክፈት የሚያስችለው ስራ በቀጣይ የሚታይበት ሁኔታ እንደሚኖር ማንሳታቸውን ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቁመዋል። በተያያዘ ዜና ዛሬ ጉብኝታቸውን ጨርሰው ወደ ኢትዮጵያ የሚመለሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሳካ ጉብኝት ማድረጋቸውን ነው ወይዘሮ ሂሩት የተናገሩት። ሁለት ዓላማ የነበረው የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ውጤታማ እንደነበር አመልክተዋል። ቀደም ሲል በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሱዳን በነበራቸው የስራ ጉብኝት የሰጡትን  መመሪያና ያደረጉትን ምከክር ተግባራዊ ለማድረግ ጉብኝት እንዳደረጉም ጠቁመዋል። በተጨማሪም በሁለቱ አገሮች ድንበር አካባቢ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ለመምከርም እንደሆነ ገልጸዋል። አቶ ደመቀ መኮንን በሱዳን በነበራቸው ቆይታ ከሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሃሰን አል-በሽር ጋር ከነበራቸው ቆይታ በተጨማሪ ከሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞቶዛ ሙሳ፣ ከተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ኡስማን ሞሃመድ ዩሱፍ ኪቢር እና ከምክትል ፕሬዚዳንት ባክሪ ሃሰን ሳላህ ጋር በኢትዮጵያና ሱዳን ሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ መክረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም