ከስምሪቱ ውጪ ነዳጅ ሲያጓጉዝ ተደርሶባታል የተባለው የቦቴ አሽከርካሪ ተቀጣ

53
ነገሌ ታህሳስ 12/2011 ከተፈቀደለት ስምሪት ውጪ  46 ሺህ 516 ሊትር ነዳጅ ጭኖ ሲጓጓዝ ተደርሶበታል የተባለው የቦቴ አሽከርካሪ በገንዘብ እንዲቀጣ መወሰኑን በጉጂ ዞን የሊበን ወረዳ ፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡ የፍርድ ቤቱ ዳኛ በለጠ ታዬ እንደገለጹት ውሳኔው የተላለፈው ለአማራ ክልል ደጀን ከተማ ከጅቡቲ የተጫነ ቤንዚልና ናፍጣ ወደ ሶማሌ ክልል ፊልቱ ከተማ ሲጓጓዝ በመያዙ ነው ነዳጁ የተጫነው የታርጋ ቁጥሩ ኮድ 3  57142 ኢት ቦቴና ተጎታቹ እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ  የቀረበው የክስ ማስረጃ ጠቅሰው አስረድተዋል፡፡ በቦቴውና በተጎታቹ ተጭኖ የተገኘው 24 ሺህ 363 ሊትር ቤንዚልን እና 22 ሺህ 153 ሊትር ናፍጣ ህዳር 28ቀን 2011 ዓ.ም. ምሽት 2.ሰዓት በህዝብ ጥቆማ ነገሌ ከተማ ውስጥ መያዙን  ዳኛው አስታውቀዋል። ፍርድ ቤቱ ዛሬ በነገሌ ከተማ በዋለው ችሎት አሽከርካሪው ሞገስ አሰፋን  በ13 ሺህ ብር እንዲቀጣ እንዲሁም የተጫነው ቤንዚልና ናፍጣ ለመንግስት ውርስ እንዲሆን መወሰኑን ገልጸዋል፡፡ "ጥፋቱ ከ10 እስከ 50 ሺህ ብር የሚያስቀጣ ቢሆንም አሽከርካሪው ከዚህ በፊት የክስ ሪከርድ ስለሌለበት ቅጣቱ ቀሎለታል" ብለዋል። አስተያየታቸውን የሰጡት የጉጂ ዞን ፖሊስ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ክፍል ኃላፊ ኢንስፔክተር ገመዳ ቱሉሳ ቅጣቱ ፍትሐዊ ፣ ትክክልና አስተማሪ መሆኑን ተናግረዋል። በኢኮኖሚ አሻጥር የኑሮ ውድነትን ለማባባስ የሚደረገውን እንቅስቃሴ  ለማጋለጥ የዞኑ ህዝብ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሰሞኑን   በተፈጠረ የቤንዚል እጥረት በነገሌ ከተማ አንድ ሊትር  እስከ 80 ብር እየተሸጠ ሲሆን  የታክሲ ክፍያም ከሁለት ብር  ወደ አምስት ብር ከፍ ማለቱን ቀደም ሲል ኢዜአ  ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም