የጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል ከአንድ ወር በኋላ የተሟላ የጎብኝዎች አገልግሎት መስጠት ይጀምራል

80
አዲስ አበባ ታህሳስ 12/2011 የጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል ከአንድ ወር በኋላ በተማሏ መልኩ የኢኮ ቱሪዝም አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አስታወቀ። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትብብር በሰሜን ምዕራብ አዲስ አበባ ጉለሌና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተሞችን በማካለል የተቋቋመው የጉለሌ ዕጽዋት ማዕከል 706 ሄክታር ይሸፍናል። ከተመሰረተ ዘጠኝ ዓመታትን ያስቆጠረውና በኢትዮጵያ ብቸኛ የሆነው የዕጽዋት ማዕከል የአካባቢ ሥነ ምህዳር ጥበቃ፣ የዕጽዋት ምርምር፣ ለአገር በቀል ዕፅዋት ጥበቃና ምርምር፣ ለተግባር ተኮር ትምህርትና ቱሪዝም መዳረሻ የመሆን ዓላማ በመያዝ የተቋቋመ ነው። ማዕከሉ ከዕጽዋት ጥበቃ፣ ጥናትና ምርምር ባሻገር ንጹህ አየር የሚተነፍሱበት አረንጓዴ መናፈሻ ለተራቡት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መዳረሻ እንዲሆን በማዕከሉ ወስጥ በርካታ የቱሪስት መዳረሻ መሰረተ ልማት ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል። የማዕከሉ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ አሠፋ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ማዕከሉ ከዚህ በፊት መደበኛ ባልሆነ አሰራር ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የመዝናኛ የስፖርት ማዘውተሪያ ሆኖ ቆይቷል። ነገር ግን ከአንድ ወር በኋላ የተሟላ የኢኮ ቱሪዝም ወይም የጎብኝዎች መዳረሻ አገልግሎት በይፋ እንደሚጀምር ተናግረዋል። ነዋሪዎች ሰርጋቸውን ጫካ ውስጥ እንዲያካሂዱ፣ ከተፋፈገ ከተማ ወጥተው ንጹህ አየር እንዲምጉ፣ ለጤናቸው ስፖርት እንዲሰሩና ተማሪዎች የዕጽዋት ብዝኃ ሕይወት ተግባር ተኮር ትምህርት እንዲያካሂዱ ሙሉ አገልግሎት ይሰጠጣል ነው ያሉት። የማዕከሉ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ጌታሁን በበኩላቸው ማዕከሉ ለሀገር በቀል ዕፅዋት ጥበቃና እንክብካቤ እያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ ለጎብኝዎች የተሟላ አገልግሎት መስጠት ሲጀመር ጎብኝዎች የሚስተናገዱበት ምቹ ሁኔታ መመቻቸቱን ተናግረዋል። ከደቡብ አፍሪካው ክርስቲያን ቡሽ በመቀጠል በስፋቱ ከአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል እስካሁን ድረስ ቁጥራቸው ከ80 ሺህ በላይ ጎብኝዎች በሆነ ዜጎች ተጎብኝቷል። በተያዘው የ2011 የስራ ዘመንም 40 ሺህ ጎብኝዎችን ለማስተናገድ ዕቅድ እንዳለው አብራርተዋል። ማዕከሉ ራሱን ለማስተዋወቅ በሚገባ ባለመስራቱ በብዙዎች ዘንድ በአቅራቢያው በሚገኘው የ'መለስ ፋውንዴሽን' እንደሚጠራ ገልጸዋል። ነገር ግን የጉለሌ ዕጽዋት ፓርክና የመለስ ፋውንዴሽነ የየራሳቸው ዓላማ ያላቸው የተለያዩ ተቋማት መሆናቸውን ገልጸው፣ ማህበረሰቡ ማዕከሉን ከተጠቀሰው ተቋም ቀደምትና የራሱ አገራዊ ዓላማ ያለው መሆኑን ህብረተሰቡ እንዲረዳላቸው ጠይቀዋል። የዕፅዋት ማዕከሉ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች፣ የዕፅዋት ዝርያዎች ጥበቃና እንክብካቤ፣ የምርምርና የኢኮ ቱሪዝም እንዲሁም ተግባር ተኮር የስነ ምህዳር የዕፅዋት ሳይንስ ጥናት ላይ ትኩረት አድርጎ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ የጎብኝዎች መመላለሻ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፤ ጊዜያዊ ሽንት ቤቶች፣ አንድ ሎጅ፣ 150 መኪና ማስተናገድ የሚችል ማቆሚያ መገንባታቸውን ጠቁመዋል። በ2011 በጀት ዓመትም የስብስባ አዳራሽ፣ የጎብኝዎች መመላለሻ የውስጥ ለውስጥ እግረኛ መንገዶች፣ ዘጠኝ ሽንት ቤቶች፣ የውሃ ግድብ፣ ተጨማሪ የውስጥ ጎብኝዎች ማዕከሉንና አዲስ አበባን ሙሉ በሙሉ የሚያዩባቸው ሁለት ማማዎች ለመገንባት በጀት መያዙን ከወራት በፊት መዘገባችን ይታሳል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም