በኢትዮጵያና የአውሮጳ ኀብረት ኮሚሸን መካከል የ644 ሚሊዮን ብር ዕርዳታ ስምምነት ተፈረመ

63
አዲስ አበባ ታህሳስ 12/2011 የአውሮጳ ኀብረት ኮሚሽን ለኢትዮጵያ የጤናና ስነ-ምግብ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የሚውል የ644 ሚሊዮን ብር ዕርዳታ ሰጠ። የዕርዳታ ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ እና በኢትዮጵያ የአውሮጳ ኀብረት ኮሚሽን ተወካይ ሚስተር ኤሪክ ሀበርስ  ዛሬ ፈርመዋል። በስምምነቱ መሰረት በእርዳታ የተገኘው ገንዘብ በኢትዮጵያ ዕድሚያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት፣ ሴቶችና ሴት ልጃገረዶች ላይ የሚታዩ የጤና እና ስነ-ምግብ ችግሮችን ለመከላከል ይውላል። በተለይ በአፋር፣ በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ጥራት ያለው የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል እርዳታው እገዛ እንደሚያደርግም በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገልጿል። ለመጪዎቹ አምስት ዓመታት ሥራ ላይ የሚውለውን ይህንኑ የጤናና ምግብ ፕሮግራም  ከፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ተግባራዊ የሚያደጉት የየክልሎቹ መንግስታት ናቸው። የአውሮጳ ኀብረት እና ኢትዮጵያ ላለፉት በርካታ አስርት ዓመታት ጠንካራ የትብብር ግንኙነት መስርተው ያከናወኗቸው ተግባራት የበርካታ ኢትዮጵያዊያንን ህይወት ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታው  አቶ አድማሱ ነበበ  ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅትም ሁለቱ ወገኖች የትብብር አድማሳቸውን በማስፋት በአየር ለውጥ ጉዳዮች፣ በኢንቨስትመንት፣ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ በመልካም አስተዳደር፣ በስደት መከላከል እና በሌሎች ዓለማቀፋዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ እየሰሩ መሆኑንም ሚኒስትር ዲኤታው ጠቅሰዋል። ስምምነቱ በተፈረመበት ስነ-ስርዓት ላይ በኢትዮጵያ የአውሮጳ ኀብረት ኮሚሽን ተወካይ ሚስተር ኤሪክ ሀበርስ ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ እየተገበረችው ላለው ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማስፈጸሚያ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ገልፀዋል። የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን በቅርቡ የኢትዮጵያን የጤና ዘርፍ በጀት ለማጠናከር የሚያስችል የ115 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም