ተደራጅተው ቦታ ባለማግኘታቸው መኖሪያ ቤት መስራት እንዳልቻሉ መምህራን ቅሬታቸውን ገለጹ

56
መቱ ታህሳስ 12/2011 ከሁለት ዓመታት በፊት በማህበር ተደራጅተው ያቀረቡት የቦታ ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ የመኖሪያ ቤት መስራት እንዳልቻሉ  በኢሉአባቦር ዞን የሰሌ ኖኖ ወረዳ መምህራን ቅሬታቸውን ገለጹ፡፡ መምህራኑ ለኢዜአ እንዳሉት መንግስት በማህበር ለተደራጁ መምህራን የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ እንዲሰጥ መመሪያ አስተላልፎ ነበር፡፡ ሆኖም እስካሁን ለጥያቄያቸው ምላሽ እንዳላገኙ ነው ያመለከቱት፡፡ በወረዳው የደርበታ ትምህርት ቤት መምህር ሽብሩ ብርሀኑ  በሰጡት አስተያየት በማህበር ተደራጅተው ጥያቄ ቢያቀርቡም ምንም በማያውቁት ምክንያት  እስካሁን ምላሽ ባለማግኘታቸው  ቅሬታ እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል፡፡ " ላቀረብነው ጥያቄ የሚሆን በቂ ቦታ በወረዳው ቢኖርም እስካሁን ለጥያቄያችን ትኩረት ያለመሰጠቱ ተቸግራናል"  ብለዋል፡፡ ከአደራጅ ኮሚቴ እስከ ወረዳው አስተዳደር  በተደጋጋሚ በመመላለስ ቅሬታቸውን ቢያቀርቡም እስካሁን ድረስ  ምላሽ እንዳላገኙ የገለጹት ደግሞ የብርብርሳ አንደኛ ትምህርት ቤት መምህር ጌታቸው ለገሰ ናቸው፡፡ " በማስተምርበት አካባቢ የመኖሪያ ቤት ስላልቀረበልኝ ከሌላ ወረዳ በመመላለስ የስራ ሰዓት ከማባከን በተጨማሪ ለተጨማሪ ወጪ እየተዳረኩ ነው"ብለዋል፡፡ የወረዳው መምህራን ማህበር ሊቀመንበር አቶ አብዮት ተካልኝ በበኩላቸው የሚመለከተው አካል ለመምህራኑ ጥያቄ ተገቢው ምላሽ ያለመሰጠቱ መምህራኑ በማህበሩ ላይ ያላቸው  እምነት እንዲቀንስ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አሁንም መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት  ለጥያቄያቸው ምላሽ እንደሚፈልጉ አመልክተዋል፡፡ የወረዳው አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሀኑ ከተማ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ በተቀመጠው መመሪያ መሰረት   በማህበር ተደራጅተው የቤት መስሪያ ቦታ ለሚጠይቁ መምህራን በቅርብ ግዜ ውስጥ ቦታ ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የኢሉአባቦር ዞን ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከበደ ነጋሳ በበኩላቸው ለመምህራኑ የቤት መስሪያ ለሚሰጠው ቦታ የካሳ ክፍያና ተያያዥ ችግሮች ምክንያት ሰሌ ኖኖ ጨምሮ በአንዳንድ ወረዳዎች ክፍተት መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡ የሚመለከታቸው የወረዳና የከተማ አስተዳደሮች ችግሮቹን በአፋጣኝ በመፍታት ጥያቄውን ላቀረቡ መምህራን የቤት መስሪያ ቦታ እንዲያቀርቡ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ኃላፊው እንዳሉት በዞኑ 13 ወረዳዎች 2ሺ515 መምህራን በ86 ማህበራት ተደራጅተው የቤት መስሪያ ቦታ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል በ35 ማህበራት ለተደራጁ 696 መምህራን እስካሁን ከ140ሺ ካሬ ሜትር በላይ የቤት መስሪያ ቦታ እንደተሰጠም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም