ጠንካራ የግብር ዘርፍ እንዲኖር ጠንካራ መሰረተ ልማት ያስፈልጋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

56
አዲስ አበባ ታህሳስ 12/2011 ጠንካራ የግብር ዘርፍ እንዲኖር ጠንካራ መሰረተ ልማት እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት "ግዴታዬን እወጣለሁ፣ መብቴን እጠይቃለሁ" በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደውን አገር አቀፍ የማህበረሰብ የታክስ ንቅናቄ ዛሬ በይፋ ሲያስጀምሩ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመልዕክታቸው እንዳሉት ቁሳዊ መሰረተ ልማቶችና ቁሳዊ ያልሆኑ እንደ ዴሞክራሲ፣ ፍትህ፣ ጸጥታና የመሳሰሉት መሰረተ ልማቶች እጅግ በጣም ወሳኝ ናቸው። "ዜጎች በሚከፍሉት ግብር መንግስት መሰረተ ልማቶች በማስፋፋት፣ የግሉ ዘርፉ ጠንካራና ተወዳዳሪ እንዲሆን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል" ብለዋል። ጠንካራና ተወዳዳሪ የሆነ የግል ዘርፍም ለዜጎች ሰፊ የስራ ዕድል ከመፍጠር በላይ ትርፋማነቱን የሚያረጋግጥና ለመንግስትም ትልቅ የገቢ ምንጭ በመሆን የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የተጀመረውን ሰፊ የዴሞክራሲ ግንባታ ለማስቀጠል ጠንካራና ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማትን በመገንባት የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚቻል ጠቁመዋል። "ያለበቂ ተሳትፎና ውክልና ግብር የመክፈል ግዴታ ሊኖር አይችልም" ያሉት ዶክተር ዐቢይ "ግለሰባዊ የመብት አያያዝ፣ ማህበረሰባዊ ደህንነት፣ የዳበረ የፍትህ ስርዓት፣ የላቀ የዕውቀትና ጥበብ አቅም፣ በምግብ ራስን መቻልና መሰረታዊ ጤናን ለሁሉም የማዳረስ ብቃት ሳይቋረጡና ከደረጃቸው ሳይወርዱ ማዳረስ የሚቻለው ያለማቋረጥ ግብር ለመሰብሰብ የሚችል ስርዓትና አቅም ስንፈጥር ብቻ ነው" ብለዋል። ኢትዮጵያን ለማሳደግና ሰላም እንድትሆን ለዜጎችና ለነዋሪዎች መሰረታዊ ፍላጎቶችን በበቂ ሁኔታ ለማቅረብና ድህነትን በማሸነፍ ወደብልጽግና ለመገስገስ ከተፈለገ ስለግብር ያለው ደካማ አመለካከት መቀየር እንዳለበት ተናግረዋል። "ግብር የሚያጭበረብር ሰው እንደ አራዳ መቆጠሩ ቀርቶ አገርና መንግስትን እንደሚጠላ ብቻ ሳይሆን ስለራሱ ልጆች የዛሬና የወደፊት ህልውና ምንም የማይጨነቅ ሞኝ ተደርጎ ሊቆጠር ይገባል" ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ዜጎችና ነዋሪዎች ግብር በመክፈል አገሪቱን፣ መንግስትንና ልጆቹን እንደሚወድ በይፋ የሚያሳይ ኩሩ ዜጋ መፍጠር እንደሚያስፈልግም አክለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም