የባህልና ቱሪዝም ዘርፉን ለማጎልበት በጥናትና ምርምር መደገፍ ይገባል...ወይዘሮ ፎዚያ አሚን

128
ሀዋሳ ግንቦት 17/2010 ኢትዮጵያ ያሏትን የባህልና ቱሪዝም ሀብቶች በማልማት በዘላቂነት ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማዋል ዘርፉ በጥናትና ምርምር ሊታገዝ እንደሚገባ የባህልና ቱሪዝም ሚንስትሯ ገለጹ፡፡ ሁለተኛው ሀገር አቀፍ የባህልና ቱሪዝም የጥናትና ምርምር ጉባኤ በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ አስተናጋጅነት በሆሳዕና ከተማ በመካሄድ ላይ ነው፡፡ በጉባኤው ላይ የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ፎዚያ አሚን እንዳሉት ኢትዮጵያ ያሏት እምቅ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ  መስህቦቿ  ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ልዩ ያደርጋታል፡፡ ከ80 በላይ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ያልተበረዘ ባህል፣ ዕምነት፣ ቋንቋና የአኗኗር ዘይቤዎቻቸው ህገ መንግስታዊ ዕውቅና አግኝቶ በጋራ፣ በፍቅርና በመተሳሰብ አብረው መኖራቸውን  በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡ አገሪቱ ያሏት ዘርፈ ብዙ የባህል፣ የታሪክና የተፈጥሮ ሀብቶች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲኖራቸው የባህልና ቱሪዝም ሀብቶችን በዘላቂነት በማጥናትና በማልማት ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ሚኒስትሯ እንዳሉት በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በምሁራን የሚደረጉ ጥናቶች በዘርፉ ዘላቂ ልማት ለማምጣት ከማስቻሉም በላይ በጥናትና ምርምር የተደገፉ ግብአትና የፖሊሲ መነሻ ሀሳቦች እንደሚገኙበት ጠቁመዋል፡፡ የደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አክመል መሀመድ በበኩላቸው እንዳሉት ክልሉ ብዝሀነትን በማስተናገድ ለሌሎች አካባቢዎች ተምሳሌት እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡ የክልሉ መንግስት ለባህልና ቱሪዝም ዘርፍ በሰጠው ትኩረት ቢሮው የብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦችን ባህል፣ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ቋንቋና የስነጥበብ ሀብቶችን በማጥናት፣ በማልማትና በማስተዋወቅ የበለጸገ ሕብረተሰብ ለመፍጠር እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል። የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጣሰው ገብሬ በበኩላቸው እንዳሉት፣ ዩኒቨርሲቲው የሀገሪቱ ሕዝቦች ባህል፣ ቋንቋና የማንነት መገለጫ እሴቶች በጥናትና በምርምር ተደግፈው እንዲለሙና ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ ለማድረግ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡ የባህልና የቱሪስት መስህብ ስፍራዎች ለምተው ለህዝብና ለሀገር ጥቅም እንዲውሉ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የራሳቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ "ያለንን ባህላዊ እሴት አዋደንና አስማምተን የጋራ በማድረግ ለዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲውል በምርምር የተደገፈ ሥራ መስራት ይጠበቅብናል" ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ናቸው። የትምህርት ተቋማት የባህል እሴቶች በምርምር ዳብረው ለሕብረተሰቡ ጠቃሚ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ የዜግነት ግዴታቸው መሆኑን በመረዳት ለምርምር ሥራ ይበልጥ ትኩረት ሰጥተው እንዲንቀሳቀሱ አመለክተዋል። " የጋራ ባህላዊ እሴቶች ግንባታ ለዘላቂ ልማትና ሰላም " በሚል መሪ ቃል ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ከደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እና ከክልሉ ዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ፎረም ጋር በመተባበር ያዘጋጀው መድረክ ዛሬ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። ለሁለት ቀናት በሚቆየው በእዚህ ሁለተኛው ሀገር አቀፍ የባህልና ቱሪዝም የጥናትና ምርምር ጉባኤ ላይ ከሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ምሁራን በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ጉባኤ አምና በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስተናጋጅነት በጎንደር ከተማ መካሄዱ ይታወሳል ፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም