አገር አቀፍ የወጣቶች የሰላም ንቅናቄ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

87
አዲስ አበባ ታህሳስ 11/2011 አገር አቀፍ የወጣቶች የሰላም ንቅናቄ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው አገር አቀፍ የወጣቶች የሰላም ንቅናቄ ኮንፍረንስ ዛሬ በኢትዮጵያ ብሔራዊ የስብሰባ ማዕከል እየተካሄደ ነው። የሰላም ንቅናቄ ኮንፈረንሱን በጥምረት ያዘጋጁት የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር፣ የሰላም ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ናቸው። የኮንፈረንሱ ዓላማ ወጣቶች ለአገር ለውጥና ሠላም ዘብ የሚቆሙበት፣ ለጥያቄያቸው ምላሽ የሚያገኙበት፣ ለአገር አንድነት በጋራ የሚነሱበት እና አላስፈላጊ ልዩነቶችንም እስከወዲያኛው ለማጥፋት ቃል እንዲገቡና አገራዊ አንድነትን ከወጣትነት ጋር ማዛመድ እንዲችሉ ማድረግ ነው። በኮንፈረንሱ ከመላው አገሪቱ የተውጣጡ 1ሺህ500 በላይ ወጣቶች ተሳታፊ ሆነዋል። “ወጣቶች ለአገራዊ ለውጥና ሰላም” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ በሚገኘው ኮንፈረንስ ላይ የተገኙት የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል እንደገለጹት፤ አዲሱ ትውልድ የዛሬ ባለዕዳና የነገ ተስፈኛ ነው። ዕዳውን ለመወጣትና ተስፋውን እውን ለማድረግ ለአገሩ ሰላም መቆም እንዳለበት አስገንዝበዋል። ትናንትናውን ማሰብ ብቻ ሳይሆን ወደነገ የተስፋ ጉዞ ለመድረስ ተግቶ መስራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ከ65 በመቶ በላይ የሆነው ወጣት ሃይል የነገ አገር ተረካቢ በመሆኑ አገር ለመረከብ የሚያስችል ዝግጅት ማድረግ እንደሚጠበቅበት ወይዘሮ ሙፈሪያት ጠቁመዋል። አነቃቂ ንግግሮችን በማድረግ የሚታወቁት የስነ-አዕምሮ ሀኪምና ስነ-ልቦና ምሁሩ ዶክተር ምህረት ደበበ በወጣትነት ዙሪያ ማብራሪያ አቅርበዋል። ወጣትነት የአሸናፊነት ስሜት ጎልቶ የሚወጣበት ዘመን በመሆኑ ወጣቱ መጪ ጊዜውን ብሩህ ለማድረግ ተሯሩጦ መስራት እንደሚጠበቅበት አስረድተዋል። የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ወይዘሮ የአለምፀጋዬ አስፋው፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ወጣት ታረቀኝ አብዱልጀባል እንዲሁም ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ 21 እናት አገር አቀፍ የሰላም መልዕክተኞች በኮንፈረንሱ ተገኝተዋል። ከአካል ጉዳተኞች ማህበር፣ ከወጣቶች ሊግ፣ ከወጣት የመንግስት ሠራተኞች ማህበር እና ከአርሶ አደር ወጣቶች እንዲሁም በመልካም አርዓያነት የተለዩ ወጣቶች ተሳታፊ ሆነዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም