ባንኩ በወጪ ንግዱ ለሚስተዋሉ ችግሮች መፍትሄ ለመሻት ከባለሃብቶች ጋር እየመከረ ነው

85
አዲስ አበባ ታህሳስ 11//2011 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በወጪ ንግዱ ለሚስተዋሉ ችግሮች መፍትሄ ለመሻት ከባለሃብቶች ጋር እየመከረ ነው። ባንኩ ለ7ተኛ ጊዜ በሚያካሂደው በዚህ መድረክ በወጪ ንግድ የተሰማሩ ላኪዎች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች፣ በባንኩ በኩል ያሉ ችግሮችና ሌሎች ተግዳሮቶች አቅርበው ውይይት እንደሚካሄድባቸው በመርሃ ግብሩ ተቀምጧል። ከመድረኩ የሚገኘው ግብዓትም የባንኩ ዓለም አቀፍ የንግድ አገልግሎት ቀልጣፋና በደንበኞች ፍላጎት የሚመራ ለማድረግ አጋዥ እንደሚሆን ታምኖበታል። የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ባጫ ጊና በዚሁ ጊዜ እነደተናገሩት ውይይቱ ባንኩ ለደንበኞቹ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሻሻል አስተዋጽኦ አለው። በወጪ ንግድ ተሳትፎ ውጤታማ ለመሆን እምቅ ሀብትና ታታሪ የሰው ኃይል የሚያስፈልግ በመሆኑ 'ይህን ሀብት መጠቅም የግድ ነው' ብለዋል። ለዚህ ደግሞ የባለድርሻ አካላት በየጊዜው እየተገናኙ መወያየትና መፍትሄ ማስቀመጥ አስፈላጊ በመሆኑ መድረኩ ተዘጋጅቷል ነው ያሉት። በመድረኩ ከ200 በላይ የሚሆኑ በወጪ ንግድ የተሰማሩ ባለሀብቶች የተገኙ ሲሆን የውይይት መነሻ ኃሳብ ቀርቧል፤ በቀጣይ ባለሀብቶቹ በስራዎቻቸው እያጋጠሟቸው ያሉ ተግዳሮቶችን በማቅረብ ውይይት ይካሄዳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም