ግዙፍ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን በከፊል ወደ ግል ለማዛወር ጥናት ተጀመረ

99
ታህሳስ 11/2011 መንግስት ከግዙፍ የልማት ድርጅቶች ውስጥ ያለውን ድርሻ በከፊል ወደ ግል ለማዛወር የሚያስችል ዓለም አቀፋዊ ጥናት ጀመረ። የልማት ድርጅቶችን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ወደ ግል ለማዛወር የተሰጠውን አቅጣጫ ተከትሎ በርካታ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን በገንዘብ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሀጂ ኢብሳ  ለኢዜአ ተናግረዋል። የሚኒስትሮች ምክር ቤት የፕራይቬታይዜሽን ፕሮግራሙ  የሚመራበትን የአሰራር ስርዓት የሚያመለክት መመሪያ በስራ ላይ እንዲውል በወሰነው መሰረት ሥራው ተጀምሯል ነው ያሉት። በገንዘብ ሚኒስቴር ስር ከፍተኛ ባለሙያዎች የተካተቱበት የቴክኒካልና የስትሪንግ ኮሚቴ እንዲሁም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የሚመራ የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱን ነው  አቶ ሃጂ ያብራሩት። የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዛወር መወሰኑ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዳለው  የገለፁት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪ መዚድ ናስር  ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት መደረጉም ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል። “የአንዱ ድርሻ ዋጋ ምን ያህል ነው፣ ስንት ሰው መሳተፍ አለበት የሚሉት ጉዳዮች በጥልቀት መታየት አለባቸው” ያሉት ባለሙያው የልማት ድርጅቶቹ ወደ ግል ከመዛወራቸው በፊት ትክክለኛ ሃብታቸውን አውቆ ዋጋቸውን ማውጣት እንመደሚገባም  አንስተዋል። አቶ ሀጂ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዛወር በዓለም ባንክ ባለሙያዎች የቴክኒክ ድጋፍ በገንዘብ ሚኒስቴር ስር የተቋቋመ የቴክኒክ ኮሚቴ ጥናት መጀመሩን አንስተዋል። ጥናቱ ቅድሚያ የተሰጠው ለኢትዮ ቴሌኮም ሲሆን በዘርፉ ፕራይቬታይዜሽን ለመፈፀም የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ነው አቶ ሀጂ የጠቀሱት ። ከዚህ ቀደም የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዘዋወር የሞከሩት ታንዛኒያ፣ ደቡብ አፍሪካና እንግሊዝ  ስኬታማ ያልሆኑበትን አጋጣሚ  መኖሩን የገለፁት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ጸጋዘአብ ለምለም ደግሞ ሽግግሩ በጥናት ላይ የተመሰረተና  ሂደቱም ግልፅ መሆን  አለበት ይላሉ ። አሁን የተጀመረው ጥናቱየኢትዮ የቴሌኮም ዘርፉን በከፊል ወደ ግል በማዛወር ሂደት የሌሎች ሀገራት ተሞክሮን በመዳሰስ ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማነጻጸር ጥልቅ ፍተሻ እንደሚያደርግም    አቶ ሀጂ ገልጸዋል። ጥናቱ እንደተጠናቀቀም ለፕራይቬታይዜሽን አማካሪ ካውንስል፣ ለማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ እና  ለስትሪንግ ኮሚቴ  እየቀረበ ደረጃ በደረጃ ተገምግሞ  ማክሮ ኮሚቴው  ጥናቱን ካጸደቀው በኋላ  ወደ ሽግግር እንደሚገባ  ነው ዳይሬክተሩ ያነሱት። ከጥናት በኋላም  በዓለም ደረጃ ያሉ የማወዳደሪያ መስፈርቶችን የማዘጋጀት ስራ በቴክኒክ ኮሚቴው እንደሚሰራም ገልጸዋል። የኢትዮ ቴሌኮም ጥናት ሲጠናቀቅ የባህር ትራንዚትና ሎጄስቲክ አገልግሎት ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድና ሌሎች የማምረቻና የአገልግሎት የልማት ድርጅቶችን በከፊል ለማዛወር ጥናት እንደሚጀመርም  ነው የተገለፀው። የኢኮኖሚክስ ተመራማሪው መዚድ በበኩላቸው የልማት ድርጅቶች ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት መሆናቸውና  በቀጥታ ኢንቨስትመንት መሆኑ ለውጭ ምንዛሬ ክምችት መጠናከር ፋይዳ እንዳለውም አንስተዋል። ከፍተኛ የብድር እዳ ላለባት ኢትዮጵያም ድርጅቶችን በተጠና ሁኔታ ለውጭ ድርጅቶች በከፊል ክፍት ማድርጉ የኢኮኖሚ እድገቱን እንደሚያሻሽልም  ጠቁመዋል። አቶ ጸጋዘአብ በበኩላቸው የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ዘርፍ በማዛወር ለእድገት የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት እና ኪሳራ እንዳይፈጠር በትኩረት ሊሰራ ይገባል  ብለዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም