ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ከ32 አመታት በኋላ ወደአገራቸው ተመለሱ

344
አዲስ አበባ ታህሳስ 11/2011 በደርግ ስርዓት ውስጥ ከፍተኛ የስራ ኃላፊ የነበሩት ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ከ32 አመታት በኋላ ትናንት ምሽት ወደአገራቸው ተመለሱ። በደርግ ስርዓትና በእሳቸው መካከል በተፈጠረው አለመግባባት የተነሳ ከአገር ወጥተው ከ1979 ዓ.ም ጀምሮ በአሜሪካን አገር በስደት ይኖሩ ነበር። ሻለቃ ዳዊት ቦሌ አለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴታ ብርቱካን አያኖ እንዲሁም የቀድሞ የስራ ባልደረባቸው የነበሩት ኮሎኔል ፍሰሐ ደስታና ሌሎች ወዳጆቻቸው አቀባበል አድርገውላቸዋል። ወደአገራቸው ከረጅም አመታት በኋላ ለመግባት የበቁት በኢትዮጵያ በመጣው ለውጥ እንደሆነ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል። ለውጡ መስመር እንዲይዝ የድርሻቸውን ለመወጣት እንደሚሰሩም ጠቁመዋል። ሻለቃ ዳዊት በደርግ ስርዓት ውስጥ በዕድገት በህብረት የስራና የዕውቀት ዘመቻ በአዝማችነት በእርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ምክትል ኮሚሽነርና ዋና ኮሚሽነርነት፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪነትን ጨምሮ በሌሎች ከፍተኛ ኃላፊነቶች ላይ ተመድበው ሰርተዋል። ከደርግ ስርዓት ጋር መግባባት ባለመቻላቸው ከአገር ተሰደው ሊወጡ ችለዋል። በአሜሪካ በፕሪስተን ዩኒቨርሲቲ ለአንድ አመት ጥናት አድርገው ''ሬድ ቲርስ'' በሚል ርዕስ ያሳተሙት መጽሐፍ በበርካታ የውጭና የአገር ውስጥ አንባቢዎች ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፈ መጽሐፍ ማዘጋጀታቸው ይታወቃል። መፅሐፉ በደርግ መንግስት ወቅት በኢትዮጵያ ጦርነት፣ ረሃብና አብዮት የነበረውን ገጽታ፣ ያስከተለውን ውጤት በዝርዝር ያጋለጠ ነበር። ሻለቃ ዳዊት ከሌሎች የትግል ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን 'የኢትዮጵያ ነጻ ወታደሮች ንቅናቄ' በሚል ስያሜ የሚጠራ ድርጅት በማቋቋም ከ1979 ዓ.ም ጀምሮ ደርግን ከስልጣን ለማስወገድ በተደረገ እንቅስቃሴ ተካፋይ ነበሩ። ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ስር ያሉ የተለያዩ ድርጅቶችን በመምራትና በማማከር አገልግሎት ላይ ተሰማርተው ቆይተዋል። ሻለቃ ዳዊት በአሁኑ ወቅት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በአፍሪካ የደህንነትና ጸጥታ ስጋቶች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ድርጅት መስርተው በዋና ስራ አስፈጻሚነት እያገለገሉ ይገኛሉ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም