የ3 ሰዎችን ህይወት ያጠፋው ግለሰብ 7 ወራት ብቻ ስለተፈረደበት ውዝግብ አስነሳ

97
አዳማ ታህስስ 11/2011 በአዳማ ከተማ የሶስት ሰዎችን ህይወት ባጠፋ ግለሰብ ላይ የተላለፈው የሰባት ወር ብቻ የእስር  ቅጣት ውሳኔ ውዝግብ አስከተለ ። የሟች እናት ወይዘሮ ኑኑ ሞጎስ ነሃሴ  8/2010 ዓ.ም ግለሰቡ ያለመንጃ ፈቃድ አይሱዙ መኪና እያሸከረከረ ልጃቸውን ከግንብ ጋር አጋጭቶ እንደገደለባቸው ተናግረዋል፡፡ "መኪናውን እንዲያሽከረክር አሳልፎ የሰጠው ሾፌር አብሮ ጋቢና ላይ ተቀምጦ ነበር " ያሉት ወይዘሮ ኑኑ ከእሳቸው ልጅ ጋር የሶስት ሰዎች ህይወት ያጠፋው ግለሰብ በሰባት ወር እስራት እንዲቀጣ የተላለፈው ውሳኔ አግባብነት እንደሌለው ገልጸዋል። መኪናውን አሳልፎ የሰጠው ቋሚ የአይሱዙ ሾፌር በስድስት ዓመት ሲቀጣ አደጋው ያደረሰው ግለሰብ ግን በሰባት ወር እስራት ብቻ  እንዲቀጣ መወሰኑ በሀገሪቱ ፍትህ የለም የሚያስብል ነው በማለት ቅሬታ አሰምተዋል ። ጥፋተኛው አቅም ስላለው ፍትህ አዛብቷል ብለው እንደሚያምኑ የገለፁት ወይዘሮ ኑኑ "የልጆቻችን ደም በከንቱ ፈሶ እንዳይቀር የሚመለከተው አካል ሊያግዘን ይገባል" ብለዋል ። " ደሃው ህብረተሰብ ፍትህ እያገኘ አይደለም " ያሉት ተጎጂዋ ፍትህ በገንዘብ ኃይል እያጣን ነው በማለት ጉዳዩን ከሚመረምሩት ዳኞች እስከ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት ድረስ አብቱታ ቢያቀርቡም  ሰሚ ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግረዋል። አደጋውን ያደረሰው ግለሰብ ሶስት ሰዎች ከመግደል  ውጪ በሁለት ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት ማድረሱን የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው ተጎጂ አቶ ይታገሱ አስራት ናቸው። "መንግስት ፍትህ አነግሳለሁ እያለ እኛ ፍትህ ተነፍገን ገንዘብ ያለው ወንጀለኛ ከዳኞችና ጠበቆች ጋር በመመሳጠር እየተጫወተብን ነው" ብለዋል። ልጆቻቸውን አጥተው  ፍትህ ፍለጋ  ሲንከራተቱ  አደጋውን ያደረሰው ግለስብ   የ60 ሺህ ብር ጠበቃ አቁሞ እንዲከላከል በማድረግ በሰባት ወራት እስራት ብቻ እንዲቀጣ መወሰኑ በሃዘን ላይ ሌላ ሀዘን እንደሆነባቸው ገልጸዋል፡፡ የክስ መዝገቡን  ሲመረምሩ  የቆዩት የአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ ገዘኽኝ ባራቃ እንደገለጹት አደጋውን ያደረሰው  ግለሰብ  ተሽከርካሪውን ያለ ሙያውና ያለ መንጃ ፈቃድ ሲያሽከረክር  የሶስት ሰዎች  ህይወት ማጥፋቱን በማስረጃ ተረጋግጧል ። የቅጣት  ውሳኔው የተላለፈው በአንቀፅ 543 ንዑስ አንቀፅ አንድ ሥር በተጣለው የቅጣት ማስልያ መሰረት መሆኑን አመልክተዋል። ሾፌሩ  የሙያ ብቃቱ ላልተረጋገጠ ግለሰብ በቸልተኝነት አሽከርካሪውን አሳልፎ በመስጠቱ ከላይ በተጠቀሰው  ንዑስ አንቀፅ 3 ሥር በተቀመጠው ከባድ የቅጣት ውሳኔ ስድስት ዓመት እና 6ሺህ ብር መቀጣቱን ገልጸዋል። የአዳማ ልዩ ዞን አቃብ ህግ የምርመራና ፍትህ አሰጣጥ ቡድን መሪ አቶ ጥላሁን መንግስቱ በበኩላቸው የተላለፈው ውሳኔ አግባብነት እንደሌላው ተናግረዋል፡፡ "እንዲያውም በአቃቤ ህግ የቀረበውን የክስ አንቀዕ 543 ንዑስ አንቀፅ 3 በመቀየር በቀላል የቅጣት ማስለያ  ጥፋተኛው እንዲከሰሰስ መደረጉን ከጅምሩ ቅሬታችን አሰምተናል " ብለዋል። አቶ ጥላሁን  እንዳሉት ጥፋተኛው የመንጃ ፈቃድ ኖረውም አልኖረውም መጀመሪያ በቀረበበት የከባድ ወንጀል መቀጣት ነበረበት ። " የተሰጠው ውሳኔ የፍትህ አሰጣጥ ስርዓትን  ያጎደፈ በመሆኑ ለኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠይቀናል " ሲሉ አመላክተዋል። ግለሰቡ የፈፀመው ጥፋት ከአምስት እስከ 15 ዓመት ፅኑ እስራት የሚያስቀጣ ሆኖ  ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ  በሰባት  ወራት  እንዲቀጣ መደረጉ ተገቢነት  እንደሌለውም አስረድተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም