የካማሽና ምዕራብ ኦሮሚያን የጸጥታ ችግር ለመፍታት የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ሥራ ጀመረ

100
አሶሳ ታህሳስ 11/2011 በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልሎች አጎራባች አካባቢዎችን የጸጥታ ችግር የሚፈታ ኮማንድ ፖስት ተቋቋመ፡፡ የኮማንድ ፖስቱ አባል አቶ ሰይፈዲን ሐሩን ለኢዜአ እንዳስታወቁት ኮማንድ ፖስቱ የፌደራልና የሁለቱ ክልሎች መንግሥታት፣ የአገር መከላከያ ሠራዊትና ፌዴራል ፖሊስ ያቀፈ ነው፡፡ ኮማንድ ፖስቱ የተቋቋመው በክልሎቹ አጎራባች አካባቢዎች የመሸገውን የታጠቀ ኃይል በመቆጣጠር የኅብረተሰቡን ደህንነት ለማስጠበቅ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ መቀመጫውን በአሶሳ ከተማ  የሚያደርገው ኮማንድ ፖስት፣ ከሱዳን የጸጥታ ኃይሎች ተባብሮ እንደሚሰራ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ጭምር የሆኑት አቶ ሰይፈዲን ገልጸዋል፡፡ በአጎራባች ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች የተሰማራው የታጠቀ ኃይል የክልሎቹን ሕዝቦች እንቅስቃሴ ከመገደብ ጀምሮ ያለልዩነት ጥፋት ሲፈጽም እንደነበርን አስታውሰዋል። ኃይሉ በአቋራጭ ሥልጣን የመያዝ ፍላጎት ያለውና ኪራይ ሰብሳቢ እንደሆነ የገለጹት አቶ ሰይፈዲን፣ ዋነኛ ዓላማውም አገራዊ ለውጡን ማደናቀፍ ነው ብለዋል። በተጨማሪም ኃይሉ ከየትኛውም ብሔርና የፖለቲካ ድርጅት ግንኙነት እንደሌለው ተደርሶበታል ነው ያሉት። የብሔራዊ የጸጥታና የደህንነት ምክር ቤት ውሳኔን ተከትሎ የአገር መከላከያ ሠራዊት አካባቢውን መቆጣጠሩ የኃይሉን እንቅስቃሴ አዳክሞታል ብለዋል፡፡ ታጣቂው ኃይል ተስፋ በመቁረጥ የመጨረሻ አማራጭ አድርጎ በመውሰድ ላይ አንደሚገኝ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቶንጎ አካባቢ ትናንት በሕዝብ ተሽከርካሪ ላይ ያደረሰውን ዓይነት ጥቃት ማሳያ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡ ሕዝብና መንግሥት የጥፋት ኃይሉ ወደ ሠላማዊ መንገድን ይመለሳል በሚል ለወራት በትዕግስት መጠበቃቸውን ያስታወሱት አቶ ሰይፈዲን፣ የጥፋት ኃይሉ በድርጊቱ እንዳይቀጥል ኮማንድ ፖስቱ መቋቋሙን አስታውቀዋል።  በካማሽና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች በሚገኙ አዋሳኝ በ25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከተፈቀደላቸው የጸጥታ ኃይሎች በስተቀር የጦር መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስ የማይቻልበት ቀይ መስመር አድርጎ እንደወሰነ ገልጸዋል፡፡ ይም በአካባቢው ኅብረተሰቡ ያለሥጋት ሠላማዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ በማሰብ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ከአካባቢው የተፈናቀሉ ወገኖችን ማደራጀት፣ እርቀ ሠላም ማውረድና የደረሱ ሰብሎች እንዲሰበሰቡ ይደረጋል ብለዋል፡፡ ኮማንድ ፖስቱ ሕገ-መንግሥቱን መሠረት በማድረግ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሳይፈም ሥራውን እንደሚያከናውን አቶ ሰይፈዲን ተናግረዋል፡፡ በበጀት፣ በቁሳቁስና በሌሎች ሎጂስቲክሶች የተደራጀው ኮማንድ ፖስት፣ በአጭር ጊዜ የአካባቢውን ጸጥታ ወደ ነበረበት ለመመለስ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡ በቤኒሻንጉል ና በኦሮሚያ ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች ባለፉት ሦስት ወራት በተከሰተ የጸጥታ ችግር ከ100 በላይ ሰዎች ሲሞቱ፣ በ10 ሺህ የሚቀጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸው ይታወሳል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም