በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር አካባቢ ያለው ችግር የአርሶ አደሮች ህይወት ሳይጎዳ ታሪካዊ ዳራውን ጠብቆ ይፈታል

71
ካርቱም ታህሳስ  11/2011 በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር አካባቢ ያለው ችግር የአካባቢውን አርሶ አደሮች ህይወት ሳይጎዳ ታሪካዊ ዳራውን ጠብቆ እንደሚፈታ ተገለጸ። በሱዳን ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ትናንት ማምሻውን ከሱዳን ፕሬዚዳንት ኡመር ሃሰን አልበሽር ጋር ተወያይተዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከውይይታቸው በኋላ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የውይይታቸው ትኩረት በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ሁለንተናዊ ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገር ላይ ነበር። ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ሰፊ የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ መሆኗን ያስታወሱት አቶ ደመቀ፤ ''ለውጡ ሙሉ እንዲሆን ትኩረት ተደርጎ ከሚሰራባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ነው'' ብለዋል። ጉብኝታቸውም በዚሁ ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቅሰው በውይይታቸውም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እንዲሰሩ የተቋቋሙ የጋራ ኮሚቴዎች ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ ላይ መምከራቸውን ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ በሁለቱ አገሮች ድንበር አካባቢ በጋራ ማልማትና አልፎ አልፎ የሚከሰተውን ችግር መፍታት የሚቻልበት ሁኔታ የውይይታቸው አካል እንደሆነ ጠቁመዋል። በድንበር አካባቢ የሚታየው ችግር የአካባቢውን ህዝብ ጥቅም በሚያስከብርና ታሪካዊ ዳራውን በጠበቀ መልኩ እንዲፈታ አቅጣጫ መቀመጡን አቶ ደመቀ ተናግረዋል። ዋና ትኩረቱም ድንበር ማካለል ሳይሆን በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ማረጋገጥና የአርሶ አደሩ ሰርቶ መለወጥ ላይ እንዲሆንም መስማማታቸውን ገልጸዋል። ውይይቱን የተካፈሉት የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲርዲር ሙሃመድ አህመድ በበኩላቸው በሁለቱ እህትማማች አገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር የውይይቱ ማጠንጠኛ እንደነበር ተናግረዋል። በፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አል-በሽር የሚመራው የሱዳን መንግስት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ የሚደግፍ መሆኑን ገልጸዋል። የሁለቱን አገሮች ትስስር የበለጠ በማጠናከር የቀጠናው ትስስር እንዲጎለብት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸዋል። ከውይይታቸውም መካከል የድንበር ጉዳይ አንዱ መሆኑን የገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በአካባቢው የሚፈጠረው ችግር የሁለቱ አገሮች መንግስታት ድንበሩን በአግባቡ ባለማካለላቸው የመነጨ እንደሆነም አስረድተዋል። በመሆኑም ችግሮች በተደጋጋሚ እንዳይከሰቱ በዚህ ጉዳይ ላይ እንዲሰሩ የተቋቋሙ ኮሚቴዎች ጉዳዩን መልክ ማስያዝ ላይ በአፋጣኝ እንዲሰሩ አቅጣጫ መቀመጡን ጠቁመዋል። ፕሬዚዳንት አልበሽር በቀድሞው  የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ሀዘንም ገልጸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም