የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ የታታሪነትና የጽናት ምሳሌ ናቸው-በቅርበት የሚያውቋቸው ግለሰቦች

43
አዲስ አበባ ታህሳስ 10/2011የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ የታታሪነትና የጽናት ምሳሌ መሆናቸውን ኢዜአ ያነጋራቸው እርሳቸውን በቅርበት የሚያውቁ ግለሰቦች ገለጹ። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ታህሳስ 05 ቀን2011 ዓ.ም 95ኛ የልደት በአላቸውን ሊያከብሩ ቀናት ሲቀሯቸው ይችን ዓለም ተሰናብተዋል። የእርሳቸውን ሞት ተከትሎም ዛሬ ብሄራዊ የሃዘን ቀን ሆኖ የተከበረ ሲሆን፤ በሚሊኒየም አዳራሽም ህዝባዊ ሽኝት ተደርጎላቸዋል። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ  የቀብር ሥነ ስርዓት ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች፣ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎችና ቤተሰቦቻቻው በተገኙበት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴደራል ተከናውኗል። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ ማህመት፣በተባባሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ዋና ጸሃፊ ቬራ ሴንጉዬ  እንዲሁም የተለያዩ አገሮች አምባሳደሮች በሥነ ስርዓቱ ላይ ታድመዋል። ኢዜአ ያነጋገርናቸው አስተያየት ሰጪዎች እንዳሉት፤ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ሳይታክቱ ዓላማቸውን ያሳኩ ታላቅ ሰው ናቸው። ከእርሳቸው ጋር ለ25 ዓመታት "በለም ኢትዮጵያ" ፕሮግራም አብረዋቸው የሰሩት ወይዘሮ ሳራ ሃሰን የቀድሞ ፕሬዚዳንት ስለነበራቸው የሥራ ፍቅር ይመሰክራሉ። የተጣላን በማስታረቅ ረገድ  ምትክ የማይገኝላቸው አባት እንደነበሩም አክለዋል። የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ በበኩላቸው "ከትንሹ ጋር ትንሽ፤ ከትልቁ ጋር ትልቅ ሆነው አገራቸውን ያስከበሩ"  ሲሉ ነው የገለጿቸው። የአሁኑ ትውልድ መከፋፈልን አርቆ  አገር መውደድንና ታታሪነትን ከእርሳቸው መማር እንዳለበትም ጠቁመዋል። ከቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ  ህይወት አራት መሰረታዊ ነገሮችን መማር እንደሚቻል የተናገሩት ደግሞ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ናቸው። በልጅነታቸው ያሰቡትንና የፈለጉትን እስከ መጨረሻው ህይወታቸው የፈጸሙ የጽናት ምሳሌ መሆናቸውንም ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም