በታንዛንያና በሊቢያ የነበሩ 80 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ተመለሱ

143
አዲስ አበባ  ታህሳስ 10/2011 ከኢትዮጵያ በህገ ወጥ መንገድ ወጥተው በታንዛኒያ እና በሊቢያ ይኖሩ የነበሩ 80 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ዛሬ ወደ አገራቸው ተመለሱ። ስደተኞቹ ዛሬ ረፋድ ላይ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም አቀባበል አድርገውላቸዋል። በአሁኑ ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በህገ-ወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ የወጡና በታንዛኒያ፣ በሊቢያ እና በሱዳን ለችግርና ለስቃይ የተዳረጉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ለመመለስ እየሰራ ይገኛል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በቅርቡ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ላይ ከታንዛኒያው አቻቸው ዶክተር አውጉስቲን ማሂጋ ጋር ባደረጉት ቆይታ በአገሪቱ ታስረው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እንዲፈቱ ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል። ሁለቱ አገሮች ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና ወዳጅነት ተጠቅመው 230 ኢትዮጵያውያን ክሳቸው ተቋርጦ በምህረት እንዲለቀቁ ተደርጓል። በምህረት ከተለቀቁት 230 ስደተኞች መካከል 65ቱ ከታንዛኒያ፣ 15ቱ ደግሞ ከሊቢያ ዛሬ ማለዳ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። ኢዜአ ከስደት ተመላሾቹ ጋር ባደረገው ቆይታ ኢትዮጵያውያኑ በሰው አገር በነበሩበት ወቅት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠቂ ሆነው ለአሰቃቂ ችግር ተዳርገው የነበረ ሲሆን በመንግስት ድጋፍ ለአገራቸው በመብቃታቸው ደስተኞች መሆናቸውን ተናግረዋል። ተስፋዬ ለፌቦ የተባለው ተመላሽ  ብዙ ስቃይና መከራ ማየታቸውን ከዚህ በዋላ በአገራቸው ሰርተው ለመለወጥ እንጂ ስደትን ዳግም እንደማይመኘው ተናግሯል "በጣም የከፋ ችግር ነው የደረሰብን፡፡  ከመንገዱ ጀምሮ ነው ስቃዩ ያለው ፤እኔ ባለማወቄ ችግር አጋጥሞኛል፡፡ እኔ እዚ ደርሻለው እዛ ያለውን ስቃይና ችግር ስላየሁት ወንድሞቼን ትቼ በመምጣቴ በጣም አዝኛለው፡፡  ችግር ቀምሰዋል አሁንም እየተጎዱ ነው።" ያለው ደግሞ ሌላው ከስደት ተመላሽ  ተሾመ  ተስፋዬ ነው ሙሉጌታ ሃብታሙ የተባለው የስደት  ተመላሽ በበኩሉ አገር ቤት ሰርተው  የማያውቁትን ስራ እየተገረፉ ሲሰሩ እንደነበር ጠቅሶ በአያ አራት ሰዐት ውስጥ አንዴ ብቻ ይበሉ እንደነበርና በጣም አስከፊ የኖሩ ሁኔታ እንዳለ ጨምሮ ገልጾል፡፡ በታንዛኒያ፣ በሊቢያ እና በሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ አገራቸው ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ 36 ኢትዮጵያውያን ከሊቢያ ተመልሰዋል። በተመሳሳይ ከሳዑዲ አረቢያ 2 ሺህ 250 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ አገራቸው መመለስ ችለዋል። በሱዳን በህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ታግተው የቆዩ 15 ኢትዮጵያውያን ከአገሪቱ የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ወደ አገር እንዲመለሱ ተደርጓል። ዛሬ አዲስ አበባ የገቡት ስደተኞች የህክምና ምርመራ ከተደረገላቸው በኋላ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ የሚደረግ ሲሆን በአካባቢያቸው ባሉ አደረጃጀቾችና ማቋቋሚያዎች ተደራጅተው ወደ ስራ እንዲገቡ እንደሚደረግ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት እና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመሆን ቀሪ ስደተኞችን ወደ አገራቸው ለመመለስ እየሰራ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም