የውጭ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ የሚያስችል የኦንላይን አገልግሎት ቴክኖሎጂ ይፋ ሆነ

147
አዲስ አበባ  ታህሳስ 10/2011 የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ዘርፍ በቴክኖሎጂ በመታገዝ የበለጠ ለማጎልበት የሚያስችል "IGude'' የተሰኘ የኦንላይን ድረ-ገጽ ቴክኖሎጂ ይፋ ሆነ። ቴክኖሎጂው ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ከፍተኛ ሚና የሚኖረው ሲሆን በኤሌክትሮኒክ ኢንቨስትመንት አገልግሎት የሚሰጠው ይህ የኢንተርኔት አገልግሎት የኢንቨስትመንት ዘርፉን የሚያስተዋውቅ እንደሆነ ተነግሯል። ድረ-ገፁ በኢንተርኔት ኢንቨስትመንት ማስታወቂያ ሲሆን የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽንና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የንግድና የልማት ኮንፍረንስ በጋራ መስርተውታል። የድረ-ገፁ ዋና አላማ የኢትዮጵያን ኢንቨስትመንት ዘርፍ ማስተዋወቅና በዘርፉ ቀልጣፋ አሰራር እንዲኖር ማድረግ ሲሆን በ19 ቋንቋዎች የተተረጎሙ የኢንቨስትመንት አማራጮች፣ ፖሊሲዎች፣ አሰራሮች፣ ምቹ ሁኔታዎች፣ የሚደረጉ ድጋፎችንና ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎችን የያዘ ነው። በአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታው በተቀየረ ቁጥር መረጃውም እለት በእለት የሚታደስ መሆኑንም ተገልጿል። የኢንቨስትመንት ኮሚሽነሩ አቶ ፍፁም አረጋ እንዳሉት፤ ድረ-ገፁ የአገሪቱን የኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎች ለአለም በማስተዋወቅና አዳዲስ ኢንቨስተሮችን በማምጣት ረገድ ትልቅ ሚና ይኖረዋል። ማንኛውንም ኢንቨስትመንት ነክ መረጃዎች ባለሃብቶቹ እንዲያገኙ ከማድረጉም በላይ ማወቅ የሚፈልጉትን ማንኛውንም ጥያቄ መጠየቅ፣በኢንቨስተርነት የመመዝገብና የኢንቨስትመንት ፈቃድ እስከማውጣት ያስችላቸዋል ብለዋል። ቴክኖሎጂውን ለመምራት የሚያስችል በቂ የሰው ሃይል ሰልጥኖ መዘጋጀቱን የገለጹት ኮሚሽነሩ በዘርፉ ከአሁን በፊት የነበረው የጊዜና የገንዘብ ብክነቶችንና ልማዳዊ አሰራር እንደሚቀይረው ገልጸዋል። የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀሃፊ ዶክተር ቬራ ሶንግዌ በበኩላቸው ቴክኖሎጂው በሌሎች አገሮች ውጤታማ የሆነና በተለይ ኢትዮጵያ ይህን መጀመሯ ለምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የኢኮኖሚ ትስስርም የሚጠቅም ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል። አፍሪካውያን ያላቸውን ትልቅ የኢንቨስትመንት አቅም ለማጎልበት በተቻለ መጠን በቴክኖሎጂ መታገዝ አለባቸው ያሉት ዋና ፀሃፊዋ ''ይህ በቀጣይ እናሳካዋለን ካልነው አንዱ ፕሮጀክት ነው'' ሲሉ ተናግረዋል። ዋና ፀሃፊዋ "ቻይና የኢንቨሰትመንት ዘርፉን በቴክኖሎጂ ለማስተሳሰር 3 ትሪሊዮን ዶላር ፈጅቶባት ውጤታማ ሆናለች" ሲሉ በአርአያነት ያነሱ ሲሆን ይህንን ተሞክሮ በአፍሪካ መድገም እንደሚቻል እምነታቸውን ገልጸዋል። ለዚህም በዛሬው እለት ይፋ ያደረግነው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ፕላትፎርም ቴክኖሎጂ ማሳያ መሆኑንና በቀጣይም እንደ አህጉር በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል። ይህ አሁን የተጀመረው ቴክኖሎጂ ለሌሎች አገሮች ተሞክሮ የሚሆንና የሚሰፋ መሆኑን የገለጹት ዋና ፀሃፊዋ ኢትዮጵያም ይህንኑ ለማጠናከር የቴክኖሎጂውን ዘርፍና የኢንቨስትመንቱን ዘርፍ ማጣመር እንደሚያስፈልጋት ጠቁመዋል። ቴክኖሎጂው የውጭ ኢንቨስትመንትን ብቻ ሳይሆን በአገር ውስጥ ያሉ ባለሃብቶችን አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችንም በቂ መረጃ እንዲኖራቸው በማድረግ በሚችሉት ዘርፍ ላይ እንዲሰማሩም ያደርጋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም