ካርታው ይዞታቸውን በባለቤትነት ለማልማት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው አርሶ አደሮች ተናገሩ

488

አምቦ ታህሳስ 10/2011 የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ማግኘታችን ለመሬታቸው ዋስትና በመሆኑ  በባለቤትነት ስሜት ለማልማት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው በምዕራብ ሸዋ ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡

በዞኑ ባለፉት አምስት ወራት ከ92ሺህ ለሚበልጡ አርሶ አደሮች የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ መሰጠቱ ተመልክቷል፡፡

አርሶአደር ፈይሳ ያደሳ የባኮ ወረዳ ነዋሪ  ሲሆኑ  ቀደም ሲል መሬታቸው በባህላዊ መንገድ ተለክቶ ስለተሰጣቸው በወሰን ከሚቀርባቸው ሰዎች ጋር በይገባኛል  ሲጋጩ  መቆየታቸውን ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።

አንድ ሄክታር መሬት ለሆነው ይዞታቸው ማረጋገጫ ካርታ ማግኘታቸው የራሳቸውን ቦታ ለይተው እንዲያውቁ ከማድረጉም በላይ ያጋጥማቸው የነበረውን አለመግባባት እንደፈታላቸው አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ከባለቤታቸው ጋር በነበራቸው የፍርድ ቤት ክስ ለተወሰነላቸው አንድ  ሄክታር  መሬት ካርታ በማግኘታቸው መደሰታቸውን የተናገሩት ደግሞ የዚሁ ወረዳ አርሶአደር ቢቂሌ ረጋሳ ናቸው፡፡

የህጋዊ ካርታ ባለቤት በመሆናቸው  መሬታቸውን አከራይተውም ሆነ አልምተው ለመጠቀም ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው አመልክተዋል።

የዳኖ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሚሊኪ ፈዬራ በበኩላቸው ይዞታቸው በዘመናዊ መንገድ ተለክቶ  ማረጋገጫ ካርታ በማግኘታቸው በባለቤትነት ስሜት ለማልማት መደላድል እንደሆናቸው ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት የይዞታ ማረጋገጫ ባለማግኘታቸው ከወሰንተኞቻቸው ጋር እየተገፉ ለእንግልት ተዳርገው እንደነበር የጨሊያ ወረዳ አርሶ አደር ዳኜ ብርሃኑ አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ይዞታቸው በዘመናዊ መንገድ ተለክቶ ካርታ በመውሰዳቸው ያለምን ችግር ልማቱን ለማካሄድ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡

የኖኖ ወረዳ አርሶ አደር ቢቂላ ምትኩ  እንዳሉት የተሰጣቸው ካርታው በወሰን መገፋፋት ምክንያት ይከሰት የነበረውን አለመግባባት በመፍታት ለልማት ያላቸውን ተነሳሽነትን አሳድጎላቸዋል፡፡

ባለፉት አምስት ወራት 92 ሺህ675  አርሶ አደሮች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ መሰጠቱን የዞኑ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት ገልጿል፡፡

የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ከተሰጣቸው አርሶአደሮች መካከል 19ሺህ 302 ሴቶች ናቸው፡፡

በጽህፈት ቤቱ   የገጠር መሬት ይዞታ መዝጋቢ ባለሙያ ወይዘሮ ወይንሸት ተሾመ እንደገለጹት ካርታው ተዘጋጅቶ ለባለይዞታዎች የተሰጠው  በዞኑ አስር ወረዳዎች ውስጥ ነው፡፡

በቀጣይም ያልተሰጣቸውን በመለየት በተመሳሳይ እንደሚከናወን አመልክተው ቀደም ሲል የነበረው አሰራር ግምታዊ ስለነበር ባለሃብቶች ከተፈቀደላቸው ይዞታ በላይ መሬት እንደሚይዙ  አውስተዋል፡፡

ይህም በአርሶ አደሮችና በባለሃብቶች መካከል ግጭት ሲፈጠር መቆየቱን የጠቀሱት ባለሙያው ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት  ይዞታን የመለካትና  ካርታ የማዘጋጀ ስራው አሁንም እንቀጠለ ነው፡፡

ባለሙያው እንዳሉት መሬቱን በዘመናዊ መንገድ መለካቱ በአርሶ አደሮች እርስ በርስና በባለሃብቶችም መካከል ይፈጠር የነበረውን አለመግባባት ችግር  ይፈታል፤ ሙስናን ለማስቀረትም ያግዛል፡፡

በምዕራብ ሸዋ  ባለፉት ዓመታት 124ሺህ 704 ለሚሆኑ አርሶ አደሮች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ መሰጠቱን ከዞኑ የመሬትና አካባቢ ጥበቃ ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡