በአማራ ክልል ዘንድሮ 945 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ይለማል

68
ባህርዳር ታህሳስ 10/2011 በአማራ ክልል በያዝነው ዓመት 945 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ እንደሚለማ የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ። ባለፉት ሁለት ወራት ከ223 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በገበያ ተኮር ምርቶች ለምቷል። አርሶ አደሮች የመስኖ ልማት ኑሮአቸውን ለማሻሻልና የምግብ ክፍተታቸውን ለመሙላት አስችሎናል ይላሉ። በቢሮው የመስኖ አጠቃቀም ባለሙያ አቶ ተሻለ አይናለም  በዘንድሮው የበጋ ወራት ልማቱን ለማካሄድ የእርሻና የዘር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አስታውቀዋል። በልማቱ የሚሳተፉት ሁለት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን አርሶ አደሮች በበጋ ወራት እስከ ሁለት ጊዜ በማልማት 144 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይሰብስባሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል። በልማቱ አርሶ አደሩ በግብርና ባለሙያዎች እየታገዘ ዕምቅ የውሃ ሃብትን ጥቅም ላይ ለማዋል  ጥረት እንደሚደረግ አስረድተዋል። ከጥቅምት ወር ጀምሮ በተካሄደ የመስኖ ልማት  ከ223 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በገበያ ተኮር ምርቶች መልማታቸውን አቶ ተሻለ ገልጸዋል። በእስካሁኑ እንቅስቃሴ የዕቅዱን 23 ነጥብ 6 በመቶ መሬት በጓሮ አትክልት፣ በአዝርዕት፣ በቅመማ ቅመምና ሰብል ለምቷል ብለዋል። እንዲሁም 140 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ መዋላቸውን ባለሙያው አስታውቀዋል። የክልሉ አንዳንድ አርሶ አደሮች ከዝናብ ጥገኝነት ተላቀው በመስኖ ልማት በመሳተፋ ኑሮአቸው እየተሻሻለና የምግብ ችግራቸው እየተፈታ መሆኑን ተናግረዋል። በባህርዳር ዙሪያ ወረዳ የይጎማ ሁለቱ ቀበሌ አርሶ አደር ተወልኝ ደሌ በበኩላቸው በመስኖ ልማት መሳተፍ ከጀመሩ ከ10 ዓመታት በላይ እንደሆናቸው ይገልጻሉ።በየዓመቱ እስከ 150 ሺህ ብር ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል። ዘንድሮም ሁለት ሄክታር የሚጠጋ መሬታቸውን በሽንኩርት፣ ቃሪያ፣ ቲማቲምና በሰብል በማልማት እስከ 180 ሺህ ብር ገቢ አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁም አስረድተዋል። በመስኖ ልማት መጠቀም ከጀመሩ ዘንድሮ አራተኛ ዓመት እንደሞላቸው ደግሞ በአዊ ዞን ዳንግላ ዙሪያ ወረዳ የብራቃት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ዋሲሁን አምሳል ናቸው። በቀበሌያቸው የተገነባው የግዛኒ መስኖ ልማት ግድብ ሥራ በመጀመሩ በመሬታቸው ገብስና የጓሮ አትክልት አልምተው የምግብ ችግራቸውን ለማሟላት እንዳስቻላቸው ገልጸዋል። በዞኑ የጓጉሳ ሽኩዳድ ወረዳ የወንጀላ ቀበሌ አርሶ አደር ሃብቴ አበራ የምርት ግብዓቶችን ተጠቅመው የቢራ ገብስና  የጓሮ አትክልት በማልማት በዓመት እስከ 40 ሺህ ብር ገቢ በማግኘት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። ዘንድሮም “አመቺ የገበያ ወቅት ከተገኘ ከመስኖ ልማት እስከ 60 ሺህ ብር ገቢ ከወጪ ቀሪ አገኛለሁ ብዬ እጠብቃለሁ” ብለዋል። በክልሉ ባለፈው በጋ ወራት በመስኖ ከለማው 837 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት 133 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተሰብስቧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም