የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ግርማ የህይወት ተሞክሮ ትውልዱ ሊማርበት የሚገባ ነው

177
አዲስ አበባ ታህሳስ 10/2011 የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ የህይወት ተሞክሮ ትውልዱ ሊማርበት የሚገባ ሰፊ ተሞክሮ እንደሆነ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች አመለከቱ። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ አስከሬን ትናንት መኖሪያ ቤታቸው ሲደርስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን 4ኛው ፓትሪያርክ አቡነ መርቆሪዮስን ጨምሮ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ዲፕሎማቶችና ወዳጅ ቤተሰቦቻቸው ተገኝተው በተዘጋጀው የሃዘን መግለጫ መዝገብ ላይ ሃዘናቸውን ገልጸዋል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም እንደገለጹት፤ አገርንና ህዝብን በቅንነት፣ በጀግንነትና በታታሪነት ከማገልገል የሚበልጥ ነገር የለም። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ሳይሉ ሙሉ ጊዜያቸውን በመስጠት አገራቸውን ማገልገላቸውን ገልጸው ትውልዱና በየደረጃው ያለው አመራር ትምህርት መውሰድ እንዳለበት አስገንዝበዋል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው በአረንጓዴ ልማትና በተለያዩ መስኮች ሰፊ ስራ የሰሩት አቶ ግርማ ለኢትዮጵያውያን ታላቅ ክብር እንደነበራቸው አስታውሰዋል። ''አገርንና ህዝብን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገልን ከቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ በመማር ሙሉ ጊዜያችንን ሰጥተን በማገልገል አገር መገንባት አለብን'' ብለዋል። የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ የጥልቅ ዕውቀት ባለቤትና መካሪ እንደነበሩ ተናግረዋል። ከአቶ ግርማ ያገኙት ምክር ለስራቸው መቃናት አስተዋጽኦ እንደነበረው አቶ ኃይለማርያም አስታውሰዋል። ዶክተር ሙላቱ በበኩላቸው አቶ ግርማ ከነበራቸው ሰፊ ተሞክሮና ልምድ ብዙ ምክር ይቀበሉ እንደነበር ተናግረዋል። የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እንዳሉት˝ አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ እንደ አባትም ናቸው ፣ የራሳቸው የግል ህይወት ተሞክሮም አገራቸውንና ህዝባቸውን በማገልገልም  በጣም ሰፋ ያለ ተሞክሮ ከሳቸው እንቀበል ነበር ፤የተሰማን ሃዘን ጥልቅ ቢሆንም ሁልጊዜ የምናስታውሳቸው ይሆናል ˝ብለዋል። የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ በተወለዱ በ95 ዓመታቸው ነው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት። አቶ ግርማ  አምስት ልጆችን አበት ነበሩ እና ከ1994 እስከ 2006 ዓም የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት በመሆን አገልገለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም