ለሐረር ከተማ ውሃ እጥረት መንግሥት መፍትሄ እንዲፈልግ ነዋሪዎች ጠየቁ

63
ሐረር ታህሳስ 10/2011 የሐረር ከተማን የንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረት ለማቃለል መንግሥት መፍትሄ እንዲፈልግላቸው ነዋሪዎች ጠየቁ። የሐረሪ ክልል ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን በከተማው ሁሉም ቀበሌዎች ውሃ ለማዳረስ እየተንቀሳቀስኩ ነው ብሏል። የተማው ነዋሪዎች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት መንግሥት ለከተማው የውሃ እጥረት በመፈተሽ ለሕዝቡ ችግር ምላሽ ሊሰጥ ይገባል። ከአስተያየት ሰጪዎቹ ወይዘሮ የሻረግ ሰይፉ የተባሉ የቀበሌ 13 ነዋሪ የከተማው የውሃ አቅርቦት እንደሚቃለል ሲነገር እንጂ፣ ሲፈታ እንደማይታይ ይናገራሉ።በመኖሪያ ቤታቸው ውሃ ካገኙ አንድ ወር እንደሞላቸውም ይገልጸሉ። በተለይም እንደ እሳቸው ባሉት ደካማና ሕመምተኛ ሰዎች ችግሩ የሚያስከትለው ጉዳት ከባድ እንደሆነም ይገልጻሉ። ወይዘሮ እንከኔለሽ በዛብህ የ43 ዓመት ጎልማሳ ናቸው።''በከተማው ውሃ ተለቋል የሚል መረጃ ቢደርሰንም፤ እስካሁን ድረስ ወደ እኛ አካባቢ ሊደርስ አልቻለም'' ነው ያሉት ። ሐረር ተወልደው ያደጉባት ከተማ መሆኗን የሚገልጹት አስተያየት ሰጪ፣''ቀደም ባሉት ዓመታት የውሃ እጥረት ሲከሰት ከወንዝና ምንጭ ውሃ ያገኙ ነበር። በአሁኑ ወቅት አካባቢው ላይ ቤት በመሰራቱና በመድረቃቸው ችግራችንን አባብሶታል” ብለዋል። ወይዘሮ ቀለሟ ረፊራ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው በንጹህ መጠጥ ውሃ ፍለጋ ውሃ ከአካባቢያቸው ርቀው ለመሄድ መገደዳቸውን ይገልጻሉ።ይህም ጊዜ አጠቃቀም ላይ ጫና ማሳደሩንይገልጻሉ። መንግሥት ችግሩ በሴቶች ላይ እያሳደረ ያለውን ጫና ለማቃለል እገዛ ሊያደርግ ይገባዋል ይላሉ። በከተማው ባለው እጥረት አንድ ጀሪካን ውሃ ከ15 እስከ 20 ብር እየተሸጠ መሆኑን የሚናገሩት ወይዘሮ ቀለሟ፤በዚያ ዋጋ የሚገዛው ውሃ ንጽህናው ባለመጠበቁ በጤና ላይ ጉዳት የሚያስከትልበት ሁኔታ እንደሚያጋጥምም ያስረዳሉ። የውሃ አቅርቦት እጥረት የሆቴልና የምግብ አገልግሎት የሚሰጡ ሥራቸውን እንድናቆም አድርጎናል የሚሉት በአነስተኛ የምግብ አገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩት አቶ ሰይፈዲን ዓሊ ናቸው።ለችግሩ መንግሥት ሊፈልግለት ይገባል ሲሉም ሐሳባቸውን ይሰጣሉ። የኢዜአ ጋዜጠኛ በከተማው ተዘዋውሮ እንደተመለከተው በተለይ በቀበሌ 13፣10ና 08 የውሃ አቅርቦት አለመኖሩን ተመልክቷል።በአንጻሩ በቀበሌ 10፣18ና 14 ውሃ በ15 ቀን አንዴ እንደሚያገኙ ከነዋሪዎች ተገልጸለታል። የሐረሪ ክልል ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ሥራ አስኪያጅ አቶ ተወለዳ አብዶሽ በከተማው የንጹህ መጠጥ ውሃን ለሁሉም ቀበሌዎች ለማዳረስ ከድሬዳዋ አስተዳደር በተዘረጋው መሥመርና ከሐረማያ ኢፋ ባቴ በሁለት ሳምንታት አንዴ በመታደል ላይ መሆኑን አስረድተዋል። በዚህ ሳምንትም ውሃውን ላላገኙ የከተማው አካባቢዎች እንደሚዳረስ ተናግረዋል። ከአርሶ አደሩ በተነሳ የካሳ ጥያቄ መሥመሩ የተቋረጠው የኤረር ቂሌ የውሃ ፕሮጀክትን ሥራ ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። የክልሉ መንግሥት ከኔዘርላንድ መንግሥት ጋር በመቀናጀት ችግሩን በዘለቄታ ለመፍታት የከርሰ ምድር ውሃ ፍለጋና ቁፋሮ ለማካሄድ ጥናቱን ማጠናቀቁን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም