ሰላማቸውን በመጠበቅ የመጡበትን የትምህርት ዓላማ ለማሳካት እንደሚጥሩ የአምቦ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ገለጹ

60
አምቦ ታህሳስ 9/2011 የተቋማቸውን ሰላምና አንድነታቸውን  በመጠበቅ እውቀት ለመቅሰም የመጡበትን የትምህርት ዓላማ  ለማሳካት እንደሚጥሩ የአምቦ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ገለጹ፡፡ በአምቦ የኒቨርሲቲው ዋናው ግቢ ባለፈው ሳምንት ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት እልባት ለመስጠት ዓላማ ያደረገ የተማሪዎች የእርቅ ስነስርዓት ዛሬ ተካሄዷል፡፡ በእርቅ ስነ-ስርዓቱ ወቅት ተማሪዎቹ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ የገቡበትን ዓላማ ብቻ ከግብ ማድረስ እንጂ የማንም አካል መጠቀሚያ እንደማይሆኑ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው  የአፋን ኦሮሞ ትምህርት ክፍል ተማሪ አሊዩ አብዱርሃማን እንዳለው ተማሪዎች ከሌሎች ወንድሞቻቸው ጋር ተቻችለው በፍቅር መኖር ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሀገሪቱን  ዕድገትና ሰላም መሆን የማይፈልጉ አካላት በሚቀርጽላቸው እኩይ አጀንዳ ተነሳስተው ከአጠገባቸው ያለውን ወንድማቸውን መጉዳት እንደሌለባቸው ተናግሯል፡፡ " ከዛሬ ጀምሮ በብሔር ሳንከፋፈል በኢትዮጵዊነታችን ብቻ በመተሳሳብና በመፈቃቀር ዓላማችንን ከግብ እናደርሳለን " ብሏል፡፡ ሌላው በዩኒቨርሲቲው የሶሻል ወረክ ተማሪ ጥላሁን ግርማ በበኩሉ "ተማሪዎች ከስሜታዊነት በመውጣት እርስ በእርስ መተሳሰብ ይኖርብናል" ብሏል፡፡ በዛሬው ዕለት የተፈጸመው የእርቅ ስነስርዓትም ተማሪዎች በአንድ ልብ ለሀገራቸው እንዲያሥቡ የሚያደርግ መሆኑን ገልጿል፡፡ እርቀ ሰላ መካሄዱ ለአንድ ሣምንት ተቋርጦ የቆየውን  ትምህርት እንዲጀምሩ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር የገለጸው ደግሞ  የሶስተኛ  ዓመት የስታቲክስ ተማሪ ኢተፋ አብደታ ነው፡፡ ከአሁን በኋላ በዩኒቨርሲቲ ምንም ዓይነት ችግር እንዳይከሰት ተማሪዎች ተወያይተው መግባባት ላይ መደረሱን አመልክቷል፡፡ ሌላው የሶሻል ወርክ ተማሪ ጸጋ ግርማ በበኩሉ "ዛሬ በፈጸምነው ዕርቅ መሠረት እኛ ተማሪዎች ሰላማችን በራሳችን ጠብቅን ዩኒቨርሲቲ የገባንበትን ዓላማ ለማሳካት ቆርጠን ተነስተናል" ብለዋል ፡፡ የተቋማቸውን ሰላምና አንድነታቸውን በመጠበቅ  ወላጆቻውንና  ሀገራቸውን የጣሉባቸውን ታላቅ ኃላፊነት ት በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተማሪዎቹ ገልጸዋል፡፡ ከእርቅ ስነስርዓቱ ሁላቸውም በኢትዮጵያዊነት ስሜታ በመተሳሰብ በጋራ ለዓላማቸው መሳካት መረባረብ እንዳለባቸው ትምህርት የወሰዱበት መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ በእርቅ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአምቦ ከተማ የሀገር ሽማግሌ ኮማንደር ሸንተማ በንቲ ባስተላለፉት መልክዕት በተማሪዎች መካካል አለመግባባት ሲፈጠር የሀገር ሽማግሌ መሃል ገብቶ ከማስታረቅ አንጻር ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዛሬ በተማሪዎች መካከል የተፈጸመውን የእርቅ ስነስርዓትን በመመልከታቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል፡፡ የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶክተር ታደሠ ቀነአ በበኩላቸው የዛሬ ሳምንት በዩኒቨርስቲው ይህ ሁኔታ እንዳልነበረና  ዛሬ ግን አብረው ተቀምጠው  መነጋገር በመቻላቸው  የሰላም አየር እንዲነፍስ መደላድል መፍጠሩን ተናግረዋል። " ስንሰማማና አንድ ስንሆን የማንችለው ነገር የለምና አንድ ሆነን ሰላማችንን እንጠብቅቅ ብለዋል። ዶክተር ታደሠ እንዳሉት  የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም የተፈጠረውን አለመግባባት በዕርቅ መፈጸማቸው ለሌሎች የሀገሪቱ  ተማሪዎችም አርዓያ ሊሆን ይገባል፡፡ ከጥል ምንም ትርፍ እንደማይገኝ የገለጹት ፕሬዘዳንቱ ተማሪዎች ከልዩነት ይልቅ አንድነታቸውን ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ እንደሚንደሚኖባቸውም አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም