የሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው ጠበቆች ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተቃወሙ

123
አዲስ አበባ ታህሳስ 9/2011 በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት የቀረቡት ቀድሞው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው ጠበቆች ፖሊስ ያቀረበውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተቃወሙ። አመልካች መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪው ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው ላይ ተጨማሪ የሙስና ወንጀል ድርጊት ማግኘቱን ትናንት ለችሎቱ አመልክቶ ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቆ ነበር። ድርጅቱ የሚያከናውናቸውን ስምምነቶች 90 በመቶ በተጠርጣሪ የሚፈጸሙ መሆኑን በመግለጽ፣ ተጠርጣሪ ቢወጡ አጠቃላይ የምርመራውን ሂደት ያደናቅፋሉ በሚል ዋስትናውን ተቋውሟል። በዛሬ በተቀጠረው ክርክርም የተጠርጣሪ ጠበቆች መርማሪ ፖሊስ ያቀረበውን የተጨማሪ ምርመራ ጊዜ ተቃውመዋል። ''መርማሪ ቀሩኝ ያላቸው ሰነዶች ከመንግስት ተቋማት የሚሰበሰቡ ናቸው፣ ውል ካለ የክፍያ ሰነዶች ይኖራሉ። ለጊዜ መጠየቂያ የቀረቡ ምክንያቶች ባለፈው ከቀረበው ጋር ተመሳሳይነት ያላቸውና አሳማኝ አይደሉም። ተጠርጣሪን አስሮ ኦዲት አላግባብ ጊዜ መጠየቅ አይገባም'' በማለት አቅርበዋል። ''የጥርጣሬ መነሻ ድርጊቶች በየጊዜው እየተጨመሩ ነው፤ አሁን እንኳን ፍርድ ቤት ሳያውቅ አምስት የወንጀል ድርጊቶች ቀርበዋል። በዚህ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መጠየቅ አይገባም'' ብለዋል። ''ኦዲት ለማስተካከል በሚል በውስጥ ሂሳብ ባለሙያዎች ኦዲት ማሰራት ተገቢ አይደለም፤ የወንጀል ድርጊቱ ከብርጋዴር ጄኔራል ጠና ቁርንዲ መዝግብ ጋር የሚመሳሰል በመሆኑ መዝገብ ሊጣመር ይገባል'' ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል። በህዳሴ ግድብና መሰል ስራዎች ላልተሰራ ስራ ክፍያ ተከፈለ በሚሉ የወንጀል ድርጊትም በተመለከተ ከመንግስት ካዝና ለመንግስት ተቋም ክፍያ ሲፈጸም ወደ ወንጀል ድርጊት እንዴት ይለወጣል ሲሉ ጠይቀዋል። ከተጠርጣሪው ጋር የማይገናኙ የወንጀል ድርጊት መነሻ አቀራረብ አለ፣ ከኦዲት በፊት ድምዳሜ እየቀደመ ነው፣ የፍትሐብሔር ጉዳይ ወደወንጀል ድርጊት ተቀይሮ እየቀረበ ነው፣ ክስ ካለ በተጠርጣሪ ላይ በአፋጣኝ ክስ መቅረብ አለበት ሲሉም ተከራክረዋል። መርማሪ ፖሊስ አዳዲስ የምርመራ ግኝቶችን ጨምሮ በአጠቃለይ በ18 የሙስና ወንጀል ድርጊቶች ተሳትፎዎችን ትናንት ይፋ አድርጎ ነበር። አመልካች መርማሪ ፖሊስ ሜቴክ ከናፍጣ ነዳጅ ማምረቻ ፋብሪካ፣ ለተሽከርካሪ፣ ለአውሮፕላን፣ ለመርከብ፣ ከሆቴል፣ ህንጻዎችና መኖሪያ ቤቶች፣ ከቆሻሻ የጀት ነዳጅ ለማምረት ግንባታ፣ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ፣ ለቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ፣ ለአዳማ እርሻ ትራክተር ማምረቻና ለሌሎች የድርጅቱ ስራዎች በተፈጸሙ ግዥዎችና ክፍያዎች ጋር በተያያዘ ከዚህ በፊት በተፈቀደለት ጊዜ ያከናወናቸውንና ቀሪ ስራዎችን በዝርዝር አቅርቧል። ከዚህም ውስጥ እአአ 2011 እና 2012 ሃይቴክ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ለተባለው የሜቴክ ድርጅት ከሲኢአይኢሲ እና ኤኤልአይቲ ከተሰኙ የቻይና ኩባንያዎች ያለ ጨረታ፣ ያለዕቅድና የግዥ ፍላጎት ዓለም አቀፍ ግዥዎች እንዲፈጸሙ በማድረግ መጠርጠራቸው ተጠቁሟል። በዚህም ከመጀመሪያው ኩባንያ ከ8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የ100 የእግረኛ ራዳሮች፣ ለሁለተኛው ኩባንያ ከ10 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለ100 እግረኛ ራዳሮች በድምሩ18 ሚሊዮን 817 ሺህ 792 ዶላር ግዥ ውል በማድረግና በማጽደቅ ያለአግባብ የመንግስትና ህዝብ ሀብት አባክነዋል በሚል ወንጀል መጠርጠራቸውን ነው ያመለከተው። ከዚህም ውስጥ ኤኤልአይቲ ከተሰኘው ኩባንያ ግዥ ከተፈጸመባቸው 100 የእግረኛ ራዳሮች 10 ተረክበው ሌሎቹ የት እንዳሉ እንደማይታወቅ ነው ያስረዳው። ከ2002 እስከ 2005 ዓ.ም በቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ከተፈጸመ ኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችና የመኪና ሞተሮች ያለጨረታና በተጋነነ ዋጋ ከ13 ኩባንያዎች ጋር ከ29 በላይ ውሎችን በማድረግና በማጽደቅ በድምሩ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዓለም አቀፍ ግዥ በመፈጸም መንግስት ከገበያ ውድድር ሊያገኝ የሚችለውን ጥቅም አሳጥተዋል ብሏል። በ2004 እና 2005 ዓ.ም የተቋሙ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ያለምንም ዓለም አቀፍ ጨረታ፣ ያለውድድር ግዥው የሚፈጸምበትን አገርና የገንዘብ መጠን አስቀድሞ በመወሰን ቴክኖትሬድስ ኤስአርኤል ከተባለ የጣሊያን ኩባንያ ጋር የ4 ሚሊዮን 450 ሺህ ዩሮ ያገለገሉ ክሬኖች ግዥ ውል በመፈጸም መንግስት ከገበያ ውድድር ሊያገኝ የሚችለውን የጥራትና ገንዘብ ጥቅም አሳጥተዋል በሚል ተጠርጥረዋል። በተመሳሳይ የግዥ ዘመንና የግዥ አፈጻጸም ፓወር ፕላስ ፒቲኢኤልቲዲ ከተባለ የሲንጋፖር ኩባንያ የ56 ሚሊዮን 943 ሺህ 800 ዶላር የኮንስትራሽን ግዥዎችን በመፈጸም የገበያ ጥራትና ገንዘብ ውድድር አሳጥተዋል በሚልም ተጠርጥረዋል። በውጭ ትምህርት ዕድል አሰጣጥ ረገድም በህጋዊ መንገድ ስለመቋቋማቸውና ተገቢው እውቅናቸው ካልተረጋገጡ ካሊፎርኒያ ኢንተርናሽናል ቴክኖሎጂና ኢስተርን ሜዲትራኒያን ዩኒቨርሲቲ ከተባሉ ተቋማት ከመመሪያ ውጭ የትምህርት ዕድል መሰጠቱን አስረድቷል። በነዚህ ተቋማትም ከ60 በላይ የሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ለማስተማር ውል በመፈጸም ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ግልጽነት በጎደለው ሁኔታ ክፍያ ተፈጽማል። ''ተቋሙም በህጋዊ መንገድ ሳይሆን በደላላ ጥቅም ትስስር የመጣ ነው፤ ከተቋሙ ሰራተኞች ውጭ ለበርካታ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና ግንኙነት ለሌላቸው ግለሰቦች በውጭ ምንዛሬ ትምሀርት እንዲማሩ ተደርጓል'' የሚሉ ጥቆማዎች ማግኘቱን መርማሪ ፖሊስ ገልጿል። የቀድሞው ዋና ዳይሬክተር የህዳሴ ግድብ የኤሌክትሮመካኒካልና የሃድሮሊክ ስራዎችን ለመስራት ከኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን በተፈረመ የ24 ቢሊዮን 400 ሚሊዮን 463 ሺህ 424 ብር ውል 23 በመቶ ብቻ አከናውኖ 65 ነጥብ 6 በመቶ ወይም ከ16 ቢሊዮን 790 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ እንዲፈጸም አድርገዋል። ኮርፖሬሽኑ ከወሰደው ውስጥም ከ7 ቢሊየን 275 ሚሊየን ብር በላይ የሚሆን ገንዘብ የት እንደደረሰ አይታወቅም ብሏል አመልካች። ከዚሁ ጋር በተተያያዘም ያገለገሉና የታለመለትን ሃይል ማመንጨት የማይችሉ አምስት ተርባይኖችን ያለጨረታ ከውጭ አገር እንዲገዙ በማድረግ በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል። ከሞሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ለግድቡ የሚሆን ሲሚንቶ እንዲቀርብ በማድርግ ከቦታ ርቀት፣ ዋጋና ጥራት አኳያ ተገቢ አይደለም፣ ግድቡ ከሚፈልገው በላይ መጠን እየቀረበ ብዙ ሺህ ኩንታል ሲሚንቶ እንዲበላሽ ተደርጓል የሚሉ ጥቆማዎችን ማግኘቱንም ለችሎቱ አስረድቷል። የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የስማርት መኪና መቆሚያ ግንባታ ለማስገንባት ሲፈልግ የሜቴክ ኃላፊዎች እኛ እንሰራዋለን በማለት ካለምንም ዋስትና የውሉን 70 በመቶ ወይም 24 ሚሊዮን ብር ሜቴክ ወስዷል፤ ይባስ ብሎም ሮኬት ሃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ ለተባለ ተቋራጭ ሰብ ኮንትራት እንዲሰጥ ተደርጎ ስራውም ሳይሰራ ገንዘቡ ተበልቶ ቀርቷል፣ ገንዘቡ እንዳይመለስ፣ ስራው እንዲሰራ ሲጠየቅ የማስፈራራት ድርጊቶች ሲፈጸሙ እንደነበር ጥቆማዎችን ማግኘቱን ገልጿል። በተመሳሳይ ቢሮው ከሜቴክ ጋር በሁለት ዙር በገባው ውል መሰረት 1 ሺህ 250 አውቶቢሶችን ለሸገርና አንበሳ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅቶች ገጣጥሞ ለመሸጥ ተስማምቶ ሲያበቃ 70 በመቶ ከፍያ ተፈጽሞለታል፣ ተጨማሪ እሴት ታክስም ትራንስፖርት ቢሮ እንዲከፍል ተደርጓል የሚልም ጥርጣሬ እንዳለውም ጠቁሟል። በነዚህና በሌሎች በአጠቃላይ በ18 የሙስና ወንጀል ድርጊቶች የሰነድ ማስረጃዎችን ለማሰባሰብ፣ ምስክሮችን ቃል ለመቀበልና ሌሎች አስፈላጊ ምርመራዎችን ለማድረግ የ14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል። ፖሊስ ትናንት ያቀረበውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ለመፍቀድ ወይም ለተጠርጣሪው ዋስትና ለመፍቀድ ችሎቱ መደበኛ ሰዓቱ በማለቁ ቀሪ ክርክሮችን ሰምቶ በጉዳዩ ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት ለአዳር ቀጠሮ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም