በጋምቤላ ክልል ለ137ሺህ ህፃናት የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ሊሰጥ ነው

60
ጋምቤላ ታህሳስ 9/2011 በጋምቤላ ክልል ከ137ሺህ ለሚበልጡ ህፃናት የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ከመጪው ዓርብ ጀምሮ በዘመቻ ሊሰጥ ነው። የክልሉ ጤና ጥበቃ  ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንድምአገኝ በላይነህ ለኢዜአ እንደገለጹት ክትባቱ ከታህሣሥ 12 ጀምሮ የጋምቤላ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ በ13 ወረዳዎች ለአንድ ሣምንት በዘመቻ ይሰጣል። እንዲሁም በክልሉ በሚገኙ ስድስት የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች እንደሚሰጥ ተናግረዋል። ክትባቱ እድሚያቸው ከስድስት ወራት ጀምሮ እስከ 15 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ለሚገኙ ህፃናት እንደሚሰጥም አቶ ወንድምአገኝ አስረድተዋል። ክትባቱ በጊዜያዊነት በተቋቋሙ የክትባት መስጪያ ጣቢያዎች፣ በትምህርት ቤቶችና በጤና ተቋማት ይሰጣል ብለዋል። ክትባቱን መስጠት ያስፈለገው በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎችና በሁለት ወረዳዎች በሽታው በወረርሽኝ መልክ በመከሰቱ ምክንያት እንደሆነም ገልጸዋል። በዘመቻው 1ሺ700 የሚጠጉ ባለሙያዎችና በጎፈቃደኞች ይሰማራሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም