በአማራ ክልል በ471 ሺህ ሄክታር መሬት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ ይካሄዳል

72
ባህር ዳር  ታህሳስ 9/2011 በአማራ ክልል በበጋ ወቅት 471 ሺህ ሄክታር መሬት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ እንደሚካሄድ የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ። በቢሮው የስነ-ህይወታዊ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ባለሙያ አቶ እስመላለም ምህረት እንደገለጹት ሥራውን ከጥር ወር አንስቶ በ6 ሺህ 400 በላይ ተፋሰሶች ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ነው። በሥራው 328 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ የማሳና የጋራ ላይ እርከን እንዲሁም ቦረቦር ማዳን ተግባራት ይከናወናሉ። የተራቆተ መሬት ደግሞ ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ በመከለል ወደነበረበት መመለስ በቀሪው መሬት እንደሚካሄድ ባለሙያው አስረድተዋል። በሥራው ይሳተፋል ተብሎ ከሚጠበቀው አራት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሕዝብ እስካሁን 75 በመቶ የሚሆነው የሰው ኃይል ተለይቶ በቡድኖች መደራጀቱን ገልጸዋል። ለሥራው የሚያስፈልግ ከሶስት ሚሊዮን የሚበልጡ ዶማ፣ አካፋና ሌሎች አነስተኛ የነፍስ ወከፍ የልማት መሳሪያዎች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። ከዞን እስከ ቀበሌ ለሚገኙ የግብርና ባለሙያዎችም ስልጠና መሰጠቱንም ባለሙያው አመልክተዋል።   በቀበሌ የተመደቡ የግብርና ባለሙያዎች  ከ316 ሺህ የሚበልጡ ቀያሽ አርሶ አደሮችን በማሰልጠን ላይ ይገኛሉ ብለዋል።   በልማቱ የሚሳተፉ አርሶ አደሮችንም ከያዝነው ወር አጋማሽ ጀምሮ በሁሉም ቀበሌዎች ኮንፈረንስ ለማካሄድ የመወያያ ሰነዶች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።   ባለፈው ዓመት 400 ሺህ ሄክታር በሚጠጋ መሬት ላይ የተከናወነው ሥራ በክረምት ወቅት በስነ-ህይወታዊ ዘዴ መጠናከሩን አስታውቀዋል።   በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰከላ ወረዳ የኮለል ለቻ ቀበሌ አርሶ አደር አማረ ላቀ በሰጡት አስተያየት ባለፉት ስምንት ዓመታት በሰራነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ አቁመው የነበሩ ምንጮች ዳግም መፍለቅ ጀምረዋል ብለዋል። ''በበጋ ወቅት የጓሮ አትክልት እያለማሁና የዛፍ ችግኝ እያዘጋጀሁ በመሸጥ በዓመት እስከ ሰባት ሺህ ብር ተጨማሪ ገቢ እንዳገኝ አግዞኛል'' ሲሉም ተናግረዋል። ያገገሙ ተፋሰሶች የእንስሳት መኖ ለማልማት እንዳስቻሏቸውም ገልጸዋል። ''አውቀንም ይሁን ሳናውቅ ያወደምነው የተፈጥሮ ሃብት ትልቅ ዋጋ እያስከፈለን ነው'' ያሉት በባህርዳር ዙሪያ ወረዳ የጎምባት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ጓዴነህ እንግዳው ናቸው። ለምነቱ በመሟጠጡ ሰብልን ለማብቀል ወደማቆም ተቃርቦ የነበረውን መሬት ከ2003 ጀምሮ በተከናወነው ሥራ የመሬታቸው ለምነት ወደነበረበት መመለሱን ተናግረዋል። ሥራው የሚያስገኘውን ጠቀሜታ በመረዳታቸው ዘንድሮ ለሚጀመረው የአፈርና ውሃ ዕቀባ ሥራ ያለቀስቃሽ ለመስራት መዘጋጀታቸውን አርሶ አደሮቹ አስረድተዋል። በክልሉ ባለፉት ዓመታት ስድስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት  በተከናወነ የተፈጥሮ ሀብት ሥራ ወደነበረበት ተመልሷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም